Sunday, November 13, 2016

በመኪና ግጭት የተጎዳው ወጣት፤ ላለፉት 50 ቀናት ራሱን እንደሳተ ነው

   ባለፈው መስከረም 7/2009 ምሽት ላይ በተለምዶ ቀራኒዮ ማዞሪያ (ካሜሮን ኤምባሲ) እየተባለ በሚጠራው አካባቢ በአንድ ግለሰብ ሆነ ተብሎ በተፈፀመ የመኪና ግጭት ጉዳት ከደረሰባቸው 3 ወጣቶች መካከል አንዱ አሁንም ራሱን እንደሳተ ነው፡፡ ወጣቱ በግጭቱ በጭንቅላቱ ላይ በደረሰበት ጉዳት ምክንያት ለወራት ሳይነቃ ሊቆይ እንደሚችል ተገልጿል፡፡ 
የ23 ዓመቱ ወጣት ዮናታን መሰለ፤ መስከረም 7/2009 ምሽት ላይ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን የአንድ ጓደኛቸውን ልደት አክብረው ወደ ቤታቸው በመመለስ ላይ እንዳሉ፣ ቴዎድሮስ ዘየደ የተባለና በአሁኑ ወቅት በእስር ላይ የሚገኝ ተጠርጣሪ ሆን ብሎና አስቦበት ዶልፊን በተባለ ተሽከርካሪ የገጫቸው ሲሆን ወጣቶቹ ላይ ከባድና ቀላል ጉዳት እንደደረሰባቸው ፖሊስ ገልጿል፡፡ 
የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የወንጀል ምርመራ ኃላፊ ዋና ሳጅን ግርማ ዱቤ እንደጠቆሙት፤ ጉዳት አድራሹ ግለሰብ በኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 9 ካሜሮን ኤምባሲ አካባቢ፣ መስከረም 7 ቀን 2009 ዓ.ም ምሽት ላይ ሆን ብሎና አስቦበት ዮናታን መሰለ፣ አብርሃም አማከል እና ዳንኤል ወልዴ በተባሉ 3 ወጣቶች ላይ የመኪና ግጭት አደጋ አድርሶባቸዋል፡፡ 

ቴዎድሮስ ዘየደ የተባለው ይኸው ተጠርጣሪ፤ በወጣቶቹ ላይ ጉዳቱን ካደረሰባቸው በኋላ ምንም አይነት እርዳታ ሳያደርግላቸው ተሽከርካሪውን ገዳመ እየሱስ በሚባል አካባቢ ሰውሮ በማቆም ራሱን ለመደበቅ ቢሞክርም፣ በነዋሪዎች ጥቆማና በፖሊስ ክትትል በቁጥጥር ሥር ሊውል ችሏል። ተጠርጣሪው ከመንገዱ ወደ ኋላ በመመለስ ሆን ብሎና አቅዶ በወጣቶቹ ላይ ያደረሰው ጉዳት እጅግ አሣዛኝ መሆኑን የጠቆሙት የምርመራ ኃላፊው፤ ሰዎች ምንም ዓይነት ግጭትና አለመግባባት ቢኖርባቸው እንኳን በዚህ መንገድ ጉዳት ማድረስ እጅግ የሚያሳዝን ተግባር ነው ብለዋል፡፡ ፖሊስ በተጠርጣሪው ላይ ክስ ለመመስረት የሚያስችለውን መረጃ ሰብስቦ እያጠናቀቀ እንደሆነ የገለፁት ኃላፊው፤ በአሁኑ ወቅት በሆስፒታል ውስጥ በከፍተኛ ህክምና ላይ የሚገኘው የአንደኛው ወጣት ዮናታን መሰለ ጉዳት ከባድ መሆኑንና የህክምና ማስረጃውን ከጉዳቱ አንፃር በቶሎ ለማግኘት አለመቻሉ ምርመራውን በጊዜ ለማጠናቀቅ እንቅፋት እንደሆነባቸው ተናግረዋል፡፡ 
ተጠርጣሪው በጊዜ ቀጠሮ በእስር ላይ የሚገኝ ሲሆን ምርምራው እንደተጠናቀቀም ክስ እንደሚመሰረትበት ጠቁመዋል፡፡ ሆን ተብሎ የሚፈፀም የተሽከርካሪ አደጋ እምብዛም ያልተለመደ መሆኑን የጠቆሙት ሃላፊው፤ አሽከርካሪዎች መኪኖቻቸውን  ለዚህ ዓይነት የወንጀል ተግባር መጠቀሚያ ከማድረግ እንዲቆጠቡም አሳስበዋል፡፡ 

የወጣት ዮናታን መሰለ ወላጅ አባት አቶ መሰለ ፍቃዱ ለአዲስ አድማስ እንደተናገሩት፤ ልጃቸው ከጓደኞቹ ጋር በባልንጀራቸው የልደት በዓል ላይ አምሽተው ወደቤት ሲመለሱ፤ የአካባቢያቸው ነዋሪ የሆነው አንድ ሌላ ወጣት ‹‹ብቻዬን ከምሆን አብሬአችሁ ልሂድ›› በማለት ተቀላቅሎአቸው በጋራ ጉዞአቸውን ይቀጥላሉ፡፡ ወጣቶቹ የአንድ አካባቢ ልጆች በመሆናቸው ሰፈራቸው ደርሰው ወደ ቤታቸው ለመግባት ከ100 ሜትር ርቀት ያነሰ ሲቀራቸው፣ በከፍተኛ ፍጥነት እየገሰገሰ፣ ወደ እነሱ የሚመጣ ዶልፊን የቤት መኪና ወጣቶቹ ላይ ይወጣባቸዋል፡፡ 
ሁኔታው ድንገተኛና ፈጣን በመሆኑ ራሳቸውን ከአደጋው መከላከል ያልቻሉት 3 ወጣቶች፤ በከፍተኛ መጠን ጉዳት ደርሶባቸዋል። ከእነዚህ ጉዳት ከደረሰባቸው ወጣቶች መካከል ደግሞ የእኔ ልጅ ዮናታን መሰለ ጉዳት እጅግ የከፋና አሳዛኝ ነው ብለዋል፡፡ 
በተክለሃይማኖት አጠቃላይ ሆስፒታል ከፍተኛ የህክምና ክትትል እየተደረገለት የሚገኘው ወጣቱ፤ እስከአሁንም ድረስ ራሱን እንደሳተ ሲሆን በጭንቅላቱ፣ በእግሮቹና በወገቡ ላይ ከባድ ጉዳት ደርሶበታል ተብሏል፡፡ 

‹‹ለልጁ የሚያስፈልገው የህክምና እርዳታ ከፍተኛ ወጪን የሚጠይቅ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በሥራ ባልደረቦቼና በቤተሰቦቹ ርብርብ ልጄ አስፈላጊውን ህክምና እንዲያገኝ እየተደረገ ነው›› ያሉት አቶ መሰለ፤ ‹‹በልጄ ላይ አደጋው ከደረሰ ጊዜ ጀምሮ በሀሳብም በገንዘብም፣ በጉልበትም የረዱኝን ሁሉ በዚህ አጋጣሚ እጅግ አድርጌ ላመሰግን እፈልጋለሁ›› ብለዋል የተጎጂው የወጣት ዮናታን አባት፡፡ የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ፖሊሶች በልጄ ላይ የተፈፀመውን ኢ-ሰብአዊ ድርጊት በመቃወም ተጠርጣሪውን ለህግ ለማቅረብ እያደረጉ ያለውን ጥረት አደንቃለሁ ያሉት አባት፤ ‹‹ላደረጉልኝ ሁሉ ከፍ ያለ ምስጋና ላቀርብ እወዳለሁ›› ብለዋል፡፡  Read more here

No comments:

Post a Comment