ሕዝብ ማንኛውንም ዓይነት ጥያቄ የማቅረብ ሕገ መንግሥታዊ መብት አለው፡፡ መንግሥትም ከሕዝብ ለሚቀርብለት ማንኛውም ጥያቄ ምላሽ የመስጠት ኃላፊነት አለበት፡፡ የጥያቄ አቀራረቡ ሕጋዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ መሆን ሲኖርበት፣ ምላሽ አሰጣጡም እንዲሁ የሕዝብን ፍላጎት ማዕከል ሊያደርግ ይገባዋል፡፡ ይህ በሠለጠነ ማኅበረሰብ ውስጥ ተግባራዊ የሚደረግ የተለመደ አሠራር ሲሆን፣ አልፎ አልፎ አለመግባባቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡ አለመግባባቶቹ ግን ከመጠን በላይ ጦዘው የሰው ሕይወት እንዳይቀጥፉ፣ የአካል ጉዳት እንዳያደርሱና የንብረት ውድመት እንዳያስከትሉ ከፍተኛ ጥንቃቄ ይደረጋል፡፡ በአገራችን ግን ይህ ዓይነቱ ሥልጡን አካሄድ ብርቅ ሆኗል፡፡ ትንሽ ኮሽ ባለ ቁጥር የሞትና የውድመት መርዶ የተለመደ ክስተት እየሆነ ነው፡፡ ይህ ዓይነት ድርጊት በአስቸኳይ መገታት አለበት፡፡ ሕዝብ በነፃነት ሐሳቡን እንዲገልጽ ይደረግ፡፡
ቅሬታዎችና ምሬቶች እየተጠራቀሙ ገደባቸውን ማለፍ ሲጀምሩ ወደ አመፅና ግጭት ሊያመሩ እንደሚችሉ ማሰብ፣ የመንግሥት ሥልጣን ከተቆናጠጠ ወገን የሚጠበቅ ኃላፊነት ነው፡፡ ማሰብ ብቻ ሳይሆን በአስቸኳይ መፍትሔ ለመፈለግ መትጋት ግዴታም ነው፡፡ ከዚያም አልፎ ተርፎ በየጊዜው ከሕዝብ ጋር መወያየትና ሕዝብን ማዕከል ያደረጉ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ጉዳይ አጀንዳዎች መቅረፅ ደግሞ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረት ከመጣል ጀምሮ የሕዝብን ዕርካታ ለመፍጠር ጠቃሚ ነው፡፡ ይህ ባለመደረጉ ግን ለዓመታት የተከማቹ ቅሬታዎች ገንፍለው እየወጡ የሰው ሕይወት እንደ ዋዛ ይቀጠፋል፡፡ የዚህች ደሃ አገር ሀብት ይወድማል፡፡ መንግሥት ከሕዝብ ጋር በመወያያቱ ለአገር ጠቃሚ የሆኑ ግብዓቶች እንዲገኙ ከማድረግ ጎን ለጎን፣ ሕዝብ የማይፈልጋቸውንና የማይመቹትን አጓጉል ድርጊቶች ለማስወገድ ይረዳል፡፡ በሐሰተኛ የካድሬ ሪፖርቶችና መረጃዎች ላይ ከመንጠላጠልና የተሳሳቱ ውሳኔዎች ላይ ከመድረስ ያድናል፡፡ የተለያዩ ሐሳቦች በነፃነት እንዲንሸራሸሩ ያግዛል፡፡ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩና እኩልነት እንዲሰፍን ጥርጊያውን ያመቻቻል፡፡
በአገሪቱ በተስተዋሉ የተቃውሞ ሠልፎች ግጭቶችና ሞት የበዙት ለዓመታት ሲንከባለሉ የነበሩ ጥያቄዎችና አቤቱታዎች የሚያዳምጣቸው በማጣታቸው መሆኑን መካድ አይቻልም፡፡ ሕዝብ ጥያቄ አለኝ ሲል በአግባቡ አዳምጦ ምላሽ መስጠት ሲገባ፣ አመፅና ብጥብጥ ለማቀጣጠል የሚረዱ ዝምታዎችና ማድበስበሶች በዝተው ይታዩ ነበር፡፡ ቅሬታዎችና ምሬቶች የሚሰሙበት መድረክ ጠፍቶ በስሜታዊነት የታጀቡ የተቃውሞ ሠልፎች ከቁጥጥር ውጪ ሲሆኑ፣ ምላሹ የከበደ ስለሚሆን የሚሰማው የሞትና የውድመት ወሬ ብቻ ነው፡፡ ሕግ ባለበት አገር ሕጋዊና በሥርዓት መቅረብ የነበረባቸው አቤቱታዎች እየተጠለፉ የግጭትና የብጥብጥ ሰበብ ይሆናሉ፡፡ ሕዝብ የራሱ ብሶት የሌለው ይመስል የውጭ ኃይሎችና ፀረ ሰላም የሚባሉት የጉዳዩ ባለቤት እንዲሆኑ ይደረጋል፡፡ ከእንዲህ ዓይነቱ ለወሬ ከማይመች አዙሪት ውስጥ በአስቸኳይ በመውጣት፣ ከሕዝብ ጋር ለዘላቂ ሰላምና መረጋጋት መነጋገር የግድ መሆን አለበት፡፡
ሕዝብ የመልካም አስተዳደር ዕጦት እንደሚያሰቃየው የታወቀ ነው፡፡ በፍትሕ መጓደል ምሬቱ ጣሪያ መንካቱ በአደባባይ የተነገረ ነው፡፡ ሙስና እንደ ሰደድ እሳት መዛመቱን ማንም አይክደውም፡፡ ማንነትን በተመለከተ የሚነሱ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍልን በተመለከተ ከፍተኛ ቅሬታ አለ፡፡ ጥቂቶች እሴት ሳይጨምሩ እየበለፀጉ ብዙኃኑ በድህነት እንደሚማቅቁ ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ በሥራ አጥነት ኑሮ የጨለመባቸው በርካታ ወጣቶች ለስደት ይዳረጋሉ፡፡ በሕገ መንግሥቱ የሕዝብና የመንግሥት መሆኑ የተረጋገጠው መሬት የወራሪዎችና የደላሎች መፈንጫ መሆኑ አገር አውርቶ የጨረሰው ጉዳይ ነው፡፡ ብቃት በሌላቸውና ግድ የለሽ ሹማምንት ምክንያት በየቦታው የሚደርሰው በደል ብዙ ተብሎበታል፡፡ እነዚህንና መሰል ብሶቶችን የተሸከመ ሕዝብ አዳማጭ አጥቶና ታፍኖ ይቀመጥ ማለት ይቻላል ወይ? አዳማጭ ያጣና የታፈነ ሕዝብ ብሶቱ ሲገነፍል የት እንደሚደርስ አይታወቅም? ወይስ ነገር ዓለሙ ተረስቷል? ሕዝብ የሚፈልገውን በነፃነት እንዲናገር መደረግ አለበት፡፡ መንግሥት በግልጽ ከሚታዩ ችግሮች ተምሮ ሕዝብን ቀርቦ በነፃነት ያወያይ፡፡ በሐሰተኛ ሪፖርት እየተመራ ሕዝብ ላይ መወሰን ይብቃ፡፡ ሕዝቡ በነፃነት የሚሰማውን ይናገር፡፡
በኦሮሚያ ክልል ከኅዳር ወር 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ከተቀሰቀሱ አመፆች እስካለፈው ሳምንት ድረስ በርካታ ዜጎች ሞተዋል፡፡ በርካቶች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ከፍተኛ የሆነ የአገር ሀብት ወድሟል፡፡ ብዙዎችም ለእስር ተዳርገዋል፡፡ መንግሥት የሕዝብን ጥያቄ በአግባቡ አድምጦ ምላሽ ባለመስጠቱ ምክንያት፣ አጋጣሚውን የተጠቀሙ ኃይሎች በማኅበራዊ ሚዲያዎች አማካይነት ብዙ ጉዳት እንዲደርስ አድርገዋል፡፡ በኦሮሚያም ሆነ በአማራ ክልሎች በተካሄዱ የተቃወሞ ሠልፎች መሣሪያ የታጠቁ ኃይሎች መታየታቸው በራሳቸው የሁኔታውን አደገኛነት ያስገነዝባሉ፡፡ ከዚያም አልፎ ተርፎ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር ተታኩሰው ጉዳት አድርሰዋል፡፡ የሕዝብ ጥያቄ በሰላማዊና በዴሞክራሲያዊ መንገድ ቀርቦ ምላሽ ማግኘት ሲገባው፣ የአመፅን መንገድ የመረጡ ኃይሎችም ጠልፈው ለራሳቸው ዓላማ ተጠቅመውበታል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አደገኛ አካሄድ በተመለደ ቁጥር ለእርስ በርስ ጦርነት፣ ከዚህ በተጨማሪም ለውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት መጋበዙ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ለዚህም ነው መንግሥት ለዘለቄታዊ ሰላም ከሕዝብ ጋር በቀጥታ መነጋገር ያለበት፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ ሕዝብ የሚያቀርባቸውን ጥያቄዎች በሙሉ የፀረ ሰላም ኃይሎችና የውጭ ኃይሎች አድርጎ መሣል ለበለጠ አደጋ ይዳርጋል፡፡ ለአገር ህልውናም ጠንቅ ነው፡፡
መንግሥትን የሚመራው ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ከሕዝብ በተጨማሪ በሰላማዊ መንገድ ተደራጅተው የፖለቲካ ትግል ከሚያደርጉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ስምምነት ይፍጠር፡፡ የተዘጋጋውን የፖለቲካ ምኅዳር ይክፈት፡፡ የማያፈናፍኑ ሕጎች እንዲላሉ፣ የመደራጀት መብትን የሚጋፉ ኢሕገ መንግሥታዊ ድርጊቶች እንዲወገዱ፣ መሠረታዊ መብቶች በሙሉ እንዲከበሩ፣ ለይስሙላ የሚነገሩ ነገር ግን በተግባር የማይታዩ አሠራሮች እንዲቆሙ፣ በአጠቃላይ የሕዝብን ነፃነትና የሕግ የበላይነትን የሚጋፉ ተግባሮችን ያስወግድ፡፡ በአደረጃጀቶቹ ላይ ብቻ እየተንጠለጠለ የሚፈጽማቸው ከሕዝብ ፍላጎት ውጪ የሆኑ ተግባራትን ገለል ያድርግ፡፡ ለሁከትና ለግጭት የሚጋብዙ መግለጫዎችንና ፕሮፓጋንዳዎችን ያቁም፡፡ ልማቱ በሕዝብ ዘንድ የባለቤትነት ስሜት መፍጠር ካልቻለ የጥቃት ዒላማ ሊሆን እንደሚችል ማወቅ ነቢይ መሆንን አይጠይቅም፡፡ ከልማቱ በፍትሐዊ መንገድ ተጠቃሚ የሆነ ዜጋ አገር አያወድምም፡፡ ነፃነቱና መብቱ የተከበረለት ዜጋ ከአመፅና ከብጥብጥ ይልቅ ለሰላማዊ መንገድ በጣም ቅርብ ነው፡፡ ጥቂቶች እየጠገቡና እየፈነጩ ብዙኃኑ መገለል ሲሰማቸው አደጋ እንዳለው መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ይህ ሁሉ በግልጽ የሚታወቀው ደግሞ ሕዝብ በነፃነት መናገር ሲችል ብቻ ነው፡፡ አፈና አገር ያፈርሳል፡፡ ነፃነት ለአገር ህልውና ይጠቅማል፡፡
በኦሮሚያም ሆነ በአማራ ክልሎች የአገር ሽማግሌዎችም ሆኑ የሃይማኖት መሪዎች ሲናገሩ የተደመጡት መንግሥት ሕዝብን በአንክሮ እንዲያዳምጥ ነው፡፡ ጥያቄ ማቅረብ መብት መሆኑን ሁሉም አስምረውበታል፡፡ የጥያቄ አቀራረቡ ሕጋዊና ሰላማዊ እንዲሆን፣ መንግሥትም በፅሞና እንዲያዳምጥ አደራ ብለዋል፡፡ የተከማቹ ጥያቄዎች ለነውጥና ለሁከት በር መክፈታቸውን አስረድተዋል፡፡ ካሁን በኋላ ችግሮች እንዳይፈጠሩ በጋራ አደራ ሲሉ ተሰምተዋል፡፡ ይኼ አደራ አገር እንዳትፈርስ፣ ሕዝብ ለትርምስና ለዕልቂት እንዳይዳረግ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱን የተቀደሰ ሐሳብ ምሁራን፣ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች፣ ሠራተኞች፣ አርሶ አደሮች፣ ወዘተ ሊጋሩት ይገባል፡፡ ከራስ ጥቅምና ፍላጎት በላይ የአገርና የሕዝብ ጥቅም እንደሚበልጥ መግባባት ያስፈልጋል፡፡ መንበረ ሥልጣንን ለማስከበር ብቻ ሲባል ሕዝብ አልሰማም ማለት አይቻልም፡፡ ሊወገዝ ይገባዋል፡፡ ሥልጣን ለመያዝ ሲባል ብቻ ደግሞ ወጣቶችን በስሜት እንዲነዱ በማድረግ አገርን ለማፍረስ መሞከርም መወገዝ አለበት፡፡ ይልቁንም እስካሁን የተመጣበት የተበላሸ የፖለቲካ ምኅዳር እንዲለወጥና ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፣ አገሪቷም የመላው ሕዝቧ የጋራ እናት መሆኗ እንዲረጋገጥ፣ ዜጎቿም በኩራት አንገታቸውን ቀና አድርገው እንዲኖሩባት፣ ከምንም ነገር በላይ ደግሞ የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥና ዘለቄታዊ ሰላም እንዲሰፍን ሕዝብ በነፃነት ሐሳቡን ይግለጽ! Read more here
No comments:
Post a Comment