Monday, August 15, 2016

ብዙዎችን ያሠጋው አተት

ረቡዕ ነሐሴ 4 ቀን 2008 ዓ.ም. ከጠዋቱ 3፡30 ሆኗል፡፡ በዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል በሚገኘው የአጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት (አተት) ሕሙማን መታከሚያ ልዩ ክፍል፣ አንድ ታዳጊ ሕፃንን ጨምሮ ስምንት ሕሙማን ተኝተው ይታከማሉ፡፡ ለአተት ሕሙማን ብቻ ተብሎ በተሰናዳው ክፍልም፣ ከሕክምና ባለሙያዎች በስተቀር አስታማሚም ሆነ ሌሎች ሰዎች መግባት አይችሉም፡፡ ምግብም ከሆስፒታሉ ይቀርባል፡፡ ቤተሰብ የሚያመጣው ካለም፣ ምግቡ በሆስፒታሉ ዕቃ እየተገለበጠ፣ አምጪው ከደጅ እንዲመለስ ይደረጋል፡፡  
በሦስት ወደተከፈለው ሕሙማኑ ክፍል ለመግባትም፣ የሕክምና ባለሙያዎቹን ጨምሮ ለመግባት የተፈቀደለት ማንኛውም አካል፣ መጫሚያው በፀረ ባክቴሪያ ተረጭቶ፣ እጁን በኬሚካል በታከመ ውኃ ታጥቦ የሚገባ ሲሆን፣ ከክፍሉ ሲወጣም ይህንኑ ድርጊት ደግሞ ይሰናበታል፡፡ ሕሙማኑ ደግሞ እንደየማገገም አቅማቸው በሕክምና ክፍሉ ለቀናት ያህል የሚቆዩ ሲሆን፣ ድነዋል ተብለው ሲወጡም፣ የለበሱት ልብስ እዚያው ይቀራል፡፡ ገላቸውን ታጥበውና ቤተሰብ የሚያቀርብላቸውን ሌላ ልብስ ለብሰው ይሰናበታሉ፡፡ ከመሰናበታቸው አስቀድሞ ግን፣ ለእነሱም ሆነ ለቤተሰብ አባላት ትምህርትና ምክር ይሰጣል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የታመመው ሰው ከሕመሙ ድኖ ከሆስፒታል ቢወጣም፣ የቤተሰቡ አባላት የግልና የአካባቢ ንፅህናቸውን ካልጠበቁ ባክቴርያው የመተላለፍ ዕድል ስላለው ነው፡፡
በሆስፒታሉ የድንገተኛ ሕመም ስፔሻሊስትና የአተት ሕሙማን ክፍል አስተባባሪ ሲስተር ስንዱ ኃይሉ እንደሚሉት፣ ክፍሉ 30 ሕሙማንን የሚይዝ ሲሆን፣ ለክፍሉም 20 ነርሶችና ሁለት ሐኪሞች ተመድበዋል፡፡ ኤምኤስኤፍ ከተባለው ግብረሰናይ ድርጅት ደግሞ፣ ስድስት ተጨማሪ ነርሶች ያገለግላሉ፡፡ ድርጅቱም የቁሳቁስና የምክር አገልግሎት ይሰጣል፡፡
የአተት ሕሙማን በጤና ጣቢያዎችም ሆነ በሆስፒታሎች ከቤተሰብና አስታማሚ ንክኪ ርቀው በሕክምና ባለሙያዎች ብቻ እየተረዱ ከሕመማቸው እንዲድኑና ከሰውነታቸው የሚወጣው ፈሳሽም በአግባቡ እንዲወገድ፣ ምግባቸውም ሆነ የግል ንፅህናቸው እንዲጠበቅ ቢደረግም፣ ከሕክምና ተቋማት ከወጡ በኋላ የሕክምና ተቋሙን ያህል ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ይቆያሉ ወይ? ሌላው የኅብረተሰብ ክፍልስ የግልና የአካባቢ ንፅህ አጠባበቁ የሠለጠነ ነው ወይ? በከተማዋ ሁሉን ኅብረተሰብ በፍትሐዊ መንገድ የግልና የአካባቢ ንፅህናውን እንዲጠብቅ የሚያስችሉ መሠረተ ልማቶች ተሟልተዋል ወይ? የአትክልትና ፍራፍሬ እንዲሁም ጥሬና የበሰሉ ምግቦች በቤትም ሆነ በሽያጭ በሚቀርቡባቸው ስፍራዎች ደህንነታቸውና ንፅህናቸው የተጠበቀ ነው ወይ? የሚሉት ጉዳዮች አነጋጋሪና እክል ያለባቸው ናቸው፡፡
ሮታቫይረስ በተባለው ባክቴርያ አማካይነት የሚከሰተው አተትም መንስኤው የግልና አካባቢ ንፅህና መጓደልና የምግብ አዘገጃጀት ጥንቃቄ የጐለው መሆን ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በአዲስ አበባ ከሰኔ 1 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ የተከሰተው አተት፣ ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ፣ በአዲስ አበባ ዙሪያና በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች ተከስቶ እንደነበረው በአጭር ጊዜ በቁጥጥር ሥር መዋል አልቻለም፡፡ በከተማዋ የጤና እክል መሆን ከጀመረም ሁለት ወራት አልፈዋል፡፡
የአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የኮሚዩኒኬሽንስ ጉዳዮች ደጋፊ የሥራ ሒደት መሪ አቶ ሙሉጌታ አድማሱ እንደሚሉት፣ ሕሙማኑን ለመርዳት በአዲስ አበባ ከሚገኙት 98 ጤና ጣቢያዎች በ29ኙ ልዩ ጣቢያ ተቋቁሟል፡፡ በዘጠኝ ሆስፒታሎች ደግሞ ከአተት በተጨማሪ ተጓዳኝ በሽታ ያለባቸው በሪፈር (በቅብብሎሽ) በመሄድ እየታከሙ ይገኛሉ፡፡ ከ29ኙ ጤና ጣቢያዎች በተጨማሪም፣ በሁሉም ጤና ተቋማት ሕሙማን ከመጡ የመጀመሪያ ዕርዳታ የሚያገኙ ሲሆን፣ ወዲያውም ወደ ልዩ ጣቢያዎቹና ወደ ሪፈራል ሆስፒታሎች ይላካሉ፡፡
በሪፈራል የአተት ሕሙማንን ከሚያስተናግዱ ሆስፒታሎች አንዱ የሆነው የዘውዲቱ መታሰቢያ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር የኔዓለም አየለ፣ በከተማዋ የወንዝ ውኃ የሚጠቀሙ ማኅበረሰቦች ላይ በሽታው መብዛቱን ይናገራሉ፡፡ የጐዳና ተዳዳሪዎችና በዝቅተኛ ደረጃ የሚኖሩ የማኅበረሰብ ክፍሎች እንዲሁም የጉልበት ሠራተኞች ከሚመጡት ሕሙማን የበለጠውን ድርሻ ይይዛሉ፡፡
ታክመው የወጡ ሰዎች ድጋሚ የሚመጡበትና ቤተሰቦቻቸውም የሚታመሙበት አጋጣሚም አለ፡፡ ይህም በባክቴርያው የተበከለ ሰገራ ከእጅ ወይም ከምግብ ተነካክቶ ወደ አፍ መግባቱንና የንፅህና አጠባበቅ መጓደሉን ያሳያል፡፡
በአተት የታመሙ ሰዎች ከየሕክምና ተቋማቱ ታክመው ቢወጡም፣ እስከ ሰባት ቀን በሽታውን ሊያስተላልፉ ይችላሉ፡፡ በመሆኑም የንፅህና ጉድለት ካለ በሽታውን መግታት አይቻልም፡፡ አቶ ሙሉጌታ እንደገለጹት፣ አንድ ሰው በአተት ተይዞ እስከ ሦስት ወር ድረስ የበሽታው ምልክት ላይታይበት ይችላል፡፡ ሆኖም በእነዚህ ጊዜያት በሽታውን ያስተላልፋል፡፡ በአተት ከሚያዙ 100 ሰዎችም 20 በመቶ ያህሉ ናቸው ምልክት አሳይተው ወደ ሕክምና የሚመጡት፡፡ በመሆኑም በሽታውን ለመከላከል ቁልፉ መፍትሔ ንፅህናን መጠበቅ ነው፡፡
በሆስፒታሉ ደረጃ መጀመሪያ ላይ የነበረው የሕሙማን ቁጥር ከፍተኛ ቢሆንም፣ አሁን ላይ እየቀነሰ መሆኑን ዶክተር የኔዓለም ይናገራሉ፡፡ ሆኖም የሕክምና ባለሙያዎች ብቻቸውን ተቆጣጥረው ሊቀንሱት ብሎም ሊገቱት አይችሉም፡፡ ኅብረተሰቡ ከእጅ መታጠብ አንስቶ ወደ አፉ ለሚገባው ምግብ ጥንቃቄ ማድረግ፣ የራሱንና የአካባቢ ንፅህናውን መጠበቅ አለበት፡፡
ዶክተር የኔዓለም እንደሚሉት፣ በአሁኑ ሰዓት በሽታውን በብዛት እያስተላለፉ የሚገኙት ሕገወጥ የጐዳና ላይ እርዶች ናቸው፡፡ ወቅቱ ዝናባማ በመሆኑም፣ ለልማት ተብለው በፈረሱ አካባቢዎች መፀዳጃ ቤቶች በአግባቡ ባለመደፈናቸው በጐርፍ እየታጠቡ አካባቢዎችን ይበክላሉ፡፡ ሕገወጥ እርዶችም በአብዛኛው የጐርፍ ውኃ በሚወርድባቸው እንዲሁም በመፀዳጃ ቤቶች ውስጥ ጭምር ስለሚከናወኑ፣ አተትን ለማስፋፋት የጐላ ሚና አላቸው፡፡ ሰው ይህንን ተገንዝቦም ጥንቃቄ ማድረግ አለበት፡፡
አተት በአብዛኛው የሚከሰተው በድርቅ በተጐዱ፣ በድህነትና በጦርነት ውስጥ በሚገኙ አካባቢዎች ነው፡፡ ጐርፍና የአየር መዛባትም በሽታውን ያስፋፉታል፡፡ አሁን ላይ ደግሞ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ተከስቷል፡፡ ይህንን አስመልክቶ ዶክተር የኔዓለም እንደገለጹት፣ አተት በዋናነት በንፅህና ጉድለት የሚነሳ ነው፡፡ በአገሪቷ ድርቅ ነበር፣ አተት ከመከሰቱ ጥቂት ቀናት ቀድሞ አዲስ አበባ ላይ ጐርፍ ተከስቷል፡፡ ድርቅ ኖሮ ጐርፍ የሚከሰት ከሆነም፣ የአተት ተዋህስያን የመሠራጨት ዕድላቸው ከፍተኛ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ጐዳና ተዳዳሪዎች የአዲስ አበባ ጐዳናዎችን ቤት አድርገውታል፡፡ ጐዳና ላይ ቤተሰብ መሥርተው የሚኖሩም አሉ፡፡ መፀዳጃቸውም እዛው ነው፡፡ መንገድ ላይ የሚቀርቡ ምግቦችም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ፣ ንፅህናቸውም እየተጓደለ ነው፡፡ ወደ ሆስፒታሉ የሚመጡትም ታሪካቸውን ሲጠየቁ፣ ከእንደዚህ ዓይነት ስፍራዎች የሚመገቡት ይበዛሉ፡፡
አተት ስላለ ብቻ ሳይሆን፣ ኅብረተሰቡ ንፅህናውን ከጠበቀና በንፅህና የተዘጋጀ ምግብ ከተመገበ፣ ከአተት በተጨማሪ ብዙ በንፅህና ጉድለት የሚመጡ በሽታዎችን ማምከን ይቻላል፡፡ ለዚህ ደግሞ መንግሥት የሚያናውነው እያንዳንዱ ሥራ የጤና ፖሊሲው ያስቀመጠውን በሽታን ቀድሞ የመከላከል አቋም ከግምት ያስገባ መሆን አለበት፡፡
የአተት በሽታን ቀድሞ ለመከላከል የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ለሠራተኞቻቸው መድሃኒት ይሰጣሉ፡፡ የሚሰጡት መድሃኒቶች አተትን በመከላከል ረገድ ያላቸውን ሚና  አስመልክተን ለዶክተር የኔዓለም ላነሳንላቸው ጥያቄ፣ አተትን ለመከላከል ከሆስፒታሉ ጋር የሚሠራው ኤምኤስኤፍም ክኒኑን እንደሚሰጥ፣ ሆኖም ክኒኑን የወሰደ ሰው በአተት ከተያዘ ሕመሙ እንዳይባባስበት ይረዳል እንጂ፣ ሙሉ ለሙሉ ከበሽታው እንደማይከላከል ነግረውናል፡፡ አንዳንድ አገሮች በተለይ የአተት አማጪን ተዋህስያን ለመከላከል ክትባት የጀመሩ ቢሆንም፣ የጐላ ጥቅም አላስገኘም፡፡ ሆኖም ለአተት የሚሰጠውን ዶክሲሳይክሊን በበሽታው ከመያዝ ቀድሞ እስከ 300 ሚሊ ግራም መውሰድ ይመከራል፡፡
አተት በዋናነት ከግልና አካባቢ ንፅህና ጉድለት የሚመጣ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ደግሞ ለአተት የሚያጋልጡ አጋጣሚዎች አሉ፡፡ በመልሶ ማልማት የፈረሱ አካባቢዎች በወቅቱ ጥቅም ላይ አለመዋላቸውና በስፍራው የነበሩ መፀዳጃዎች በአግባቡ አለመደፈናቸው፣ የዝናብ ፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች ከመፀዳጃ ቤት ጋር የተያያዙበት አካባቢዎች መኖራቸው፣ ኅብረተሰቡም ዝናብን ተገን አድርጐ የመፀዳጃ ቤት ፍሳሽ በየጐዳናው መልቀቁ፣ በየጐዳናው ላይ ያለምንም ጥንቃቄ የበሰሉ ምግቦች የሚሸጡ መሆኑ፣ ኅብረተሰቡ እጁን ታጥቦ በመመገብ ላይ ያለው ልማድ አለመዳበሩ፣ በየጐዳናው መፀዳዳቱ በቀላሉ ኅብረተሰቡን ለአተት ከሚያጋልጡትና ሥርጭቱንም ከሚያስፋፉት ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህን ማስተካከል ካልተቻለ አተት ሁሌም ሥጋት ሆኖ ይቀጥላል፡፡
ምግብ የሚያቀርቡ ሆቴሎች፣ ሬስቶራንቶችና ካፌዎች፣ ልኳንዳዎች እንዲሁም በምግብና በመጠጥ ዘርፍ የተሰማሩ ኢንዱስትሪዎችም ከትርፋቸው ባሻገር ኃላፊነት የተሞላበትና የአገሪቱን የጤና ፖሊሲ የተከተለ አቅርቦት ከሌላቸው ማኅበረሰቡን ለችግሩ ያጋልጣሉ፡፡ የሕክምና ተቋማት ቢሆኑም እንዲሁ፡፡ አገሪቷ የጣለችባቸውን ኃላፊነት ዘንግተውና ኅብረተሰቡ ያሳደረባቸውን እምነት ሸርሽረው፣ ኅብረተሰቡን ለከፋ ጉዳት የሚዳርጉ በአገሪቷ ብሎም በከተማዋ ሲናኙ ይስተዋላሉ፡፡
ከአተት ጋር በተያያዘ ብቻ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የምግብ፣ መድሃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን፣ አተት በከተማዋ ከተከሰተ ጀምሮ እስከ ሐምሌ 20 ቀን 2008 ዓ.ም. ብቻ በ37,130 የምግብና የመጠጥ አገልግሎት በሚሰጡ ሆቴል፣ ልኳንዳ፣ ጁስ ቤቶች እንዲሁም በግል ሕክምና ተቋማት ላይ ባደረገው ክትትል፣ ለአተት መስፋፋት መንስኤ የሆኑና የፅዳት ጉድለትና የሕክምና አገልግሎት ክፍተት በታየባቸው 5,414 ተቋማት ላይ ዕርምጃ ወስዷል፡፡
ዕርምጃ ከተወሰደባቸው መካከል 3,643 ሆቴል ቤቶችና 436 ልኳንዳ ቤቶች የማስጠንቀቂያና የገንዘብ ቅጣት፣ 412 የፍራፍሬና ጁስ ቤቶችና 27 የግል ጤና ተቋማት ማስጠንቀቂያ ደርሷቸዋል፡፡ ከዚህም ሌላ 704 ሆቴል ቤቶች፣ 96 ልኳንዳ ቤቶች፣ 84 የፍራፍሬና ጁስ ቤቶች እንዲሁም 12 የግል ሕክምና ተቋማት ታሽገዋል፡፡
የባለሥልጣኑ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጌታቸው ወረቴ እንደገለጹት፣ በሆቴል ቤቶች ላይ ዕርምጃው ሊወሰድ የቻለው የምግብ አቅራቢዎች የንጽህና ጉድለት፣ የምግብ ማቅረቢያዎቹና ማብሰያዎች፣ እንዲሁም የምግብ ማብሰያና መፀዳጃ ቤቶች አያያዝና አጠባበቅ ለበሽታው መስፋፋት መንስኤ ሆነው በመገኘታቸው ነው፡፡ ልኳንዳ ቤቶቹም ለእሽግ የተዳረጉት የሠራተኞች የጤና ምርመራ አለማድረግ፣ ለሽያጭ ያዘጋጇቸው ሥጋዎች ሕጋዊ እውቅና ካለውና ንጽህናው በተጠበቀ መልኩ አገልግሎት ከሚሰጡ ቄራዎች የቀረቡ አለመሆናቸው በመረጋገጡና በአንዳንድ ልኳንዳ ቤቶች ውስጥም በአተት የታመሙ ሠራተኞች በመገኘታቸው ነው፡፡ በግል ሕክምና ተቋማት ላይም ቅጣቱ ሊጣልባቸው የቻለው፣ የአተት ሕሙማን ለሕክምና ሲሄዱ የመከልከል አዝማሚያ ስለታየባቸው ነው፡፡
አቶ ጌታቸው እንደሚሉት፣ ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ በዓመት ሁለቴ የሚያደርገው የቁጥጥር ሥራ በቂ ስላልሆነ፣ ቁጥጥሩን ቀጣይ ለማድረግ ከደንብ ማስከበር ጽሕፈት ቤት፣ ከንግድ፣ ከባህልና ቱሪዝም ቢሮዎች ጋር በቅንጅት ለመሥራት የሚያስችለውን ስምምነት ተፈራርመዋል፡፡ የቁጥጥር ሥራውን የሚያከናውነውም፣ አተት ስለተከሰተ ሳይሆን በቋሚነት ይሆናል፡፡ የጤና ጉድለት ክስተቶች በልዩ ሁኔታ ሲከሰቱ ደግሞ የበለጠ ትኩረት የሚያደርግበት አሠራር ይኖረዋል፡፡ Read more here

No comments:

Post a Comment