Thursday, June 28, 2018

ኢትዮጵያና ኤርትራ በቅርቡ በመሪዎች ደረጃ ይነጋገራሉ

ኢትዮጵያና ኤርትራ በቅርቡ በመሪዎች ደረጃ ይነጋገራሉ። ኢትዮጵያና ኤርትራ በቅርቡ በመሪዎች ደረጃ ውይይት እንደሚያደርጉ ተገለፀ።
ባለፈው ማክሰኞ አዲስ አበባ የገባው የኤርትራ መንግስት ከፍተኛ ልዑክ ቡድን የኢትዮጵያ ቆይታውን ያጠናቀቀ ሲሆን፥ ዛሬ ይመለሳል።
በቆይታው ዙሪያ ዛሬ መግለጫ የሰጡት የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ሀገራቱ በመሪዎች ደረጃ በቅርቡ ውይይት እንደሚያደርጉ ነው ያስታወቁት።
አዲስ አበባ ላይ ከኤርትራ መንግስት ከፍተኛ ልዑክ ቡድን ጋር የተደረገው ውይይት እንዲመጣ ለሚፈለገው ሰላም ምቹ እድል የፈጠረ መሆኑንም ገልፀዋል።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂም ዛሬ መልዕክት ልከዋል።
የኤርትራ መንግስት ከኢትዮጵያ ጋር ገንቢ ውይይት የሚያደርግ ከፍተኛ ልዑኩን ወደ አዲስ አበባ መላኩ ይታወሳል።
በኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አቶ ኦስማን ሳለህ የሚመራው እና የፕሬዘዳንት ኢሳያስ አፍወርቂ አማካሪና የፖለቲካ ጉዳዮች ኃላፊ አቶ የማነ ገብረአብ ያካተተው ልኡክ ባሳለፍነው ማክሰኞ ነበር አዲስ አበባ የገባው ።
ለኤርትራ መንግስት ልኡካን ቡድን አዲስ አበባ ሲገቡን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በብሄራዊ ቤተ መንግስት የእራት ግብዣ አድርገውላቸዋል።
በተጨመማሪም ልኡኩ በትናንትናው እለት የኢትዮጵያን የልማት እንቅስቃሴ ለመመልከት ወደ ሀዋሳ ከተማ በማቅናት የሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክን መጎብኘቱም ይታወሳል።
የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ባሳለፍነው ሳምንት በድንበር ጉዳይ ላይ የሚነጋገር የሀገራቸውን ልዑክ ወደ አዲስ አበባ እንደሚልኩ ማሳወቃቸውን ተከትሎ ነበር ልኡኩ ወደ አዲስ አበባ የመጣው።
የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባለፈው ግንቦት ወር መጨረሻ ባካሄደው ስብሰባ የኢትዮ- ኤርትራ ወቅታዊ ሁኔታን በመገምገም፥ ኢትዮጵያ የአልጀርሱን ስምምነትና የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ተቀብላ ለመተግበር መስማማቷን መግለጹ ይታወሳል።
ይህን ተከትሎም በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል ተፈጥሮ የቆየው አለመግባባት እንዲያበቃና በሁለቱ
ወንድማማች ህዝቦች መካከል ዘላቂ ሰላም እንዲፈጠር ጥሪ ማቅረቡም የሚታወስ ነው።
በአልአዛር ታደለ

No comments:

Post a Comment