ኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች 3 ቢሊየን ዶላር መጠን ያላቸው የውጭ ምንዛሬ ድጋፍና ኢንቨስትመንት ስምምንቶችን ተፈራረሙ። የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ልዑል አልጋወራሽ ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ አል ነኸያን በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ለማድረግ አዲስ አበባ አዲስ አበባ ገብተዋል።
የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በመገኘት ለልዑል አልጋወራሽ ሼክ መሀመድ አቀባበል ያደረጉላቸው ሲሆን፥ የቦሌ ለሚ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፓርክ ግንባታ የሚገኝበትን ደረጃ በጋራ ጎብኝተዋል። በመቀጠልም በብሄራዊ ቤተመንግስት ውይይት አድርገዋል።
በውይይታቸውም ላይ የሀገራቱ የቢዝነስ፣ ኢኮኖሚ እና የህዝብ ለህዝብ ግኑኝነት እንደዚሁም አካባቢያዊ የሰላምና ፀጥታ ጉዳዮች ተነስተዋል።
ሀገራቱ በተለያዩ ዘርፎች በጋራ መስራት የሚያስችሏቸውንም በአጠቃላይ 3 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር መጠን ያላቸው የውጭ ምንዛሬ ድጋፍ እና ኢንቨስትመንት ስምምነቶችን ማምሻውን ተፈራርመዋል።
ከስምምነታቸው መካከልም ኢትዮጵያ ለተለያዩ የውጭ ምንዛሬ ጥያቄዎች ምላሽ እንደትሰጥ የሚያስችል የ1 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር የውጭ ምንዛሬ ድጋፍ ስምምነት ይገኛል።
ይህም ገንዘብ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የሚቀመጥ መሆኑም ነው የተገለፀው።
2 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላሩ ደግሞ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ባለሀብቶች በቀጥታ ኢንቨስትመንት የሚያፈሱት እንደሆነ ተመልክቷል።
ይህም ቀጥታ ኢንቨስትመንት በኢንዱሰትሪ ፓርኮች፣ በማምረቻ ፋብሪካዎች፣ በሆስፒታል፣ በሆቴልና የገበያ ማእከላት ልማት ላይ የሚውል ነው።
ሀገራቱ ኢንቨስትመንትን እና ቱሪዝምን በጋራ ለማስፋፋት እንዲሁም የዲፕሎማቲክ ቪዛን በየራሳቸው ለማስቀረት የተዘጋጁ ስምምነቶችንም ተፈራርመዋል።
ልዑል አልጋ ወራሽ ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ አል ነኸያን በቆይታቸው የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳፋኪ ጋር ይወያያሉ ተብሎም ይጠበቃል።
ከዚህ በተጨማሪም ልዑል አልጋ ወራሹ በኢትዮጵያ በሚኖራቸው የሁለት ቀናት ቆይታ የመስክ ጉብኝትም ያደርጋሉ ነው የተባለው።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በቅርቡ በተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በቆይታቸውም ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ልዑል አልጋ ወራሽ ሼክ መሀመድ ቢን አል ነኸያን ጋር በአቡ ዳቢ ተወያይተዋል።
በዚህም ወቅት ሁለቱ ሀገራት ወዳጅነታቸውን እና ትብብራቸውን የበለጠ ማጠናከር በሚችሉበት ሁኔታ እንዲሁም በወቅታዊ አካባቢያዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውም ይታወሳል።
Source: Fana
No comments:
Post a Comment