Saturday, May 26, 2018

መከላከያ ሠራዊት በኦሮሚያ ክልል ጥቃት መፈጸሙ ተገለጸ

መከላከያ ሠራዊት በኦሮሚያ ክልል ጥቃት መፈጸሙ ተገለጸ
የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ ኢሌ በኦሮሚያ እና ሶማሌ ድንበር አካባቢ ጥቃት መፈጸማቸው ተገለጸ፡፡ ይህን ድንበር ዘለል ጥቃት በመቃወም አደባባይ የወጡ የምስራቅ ሐረርጌ ነዋሪዎች በመከላከያ ሠራዊት አባላት እርምጃ እንደተወሰደባቸው መረጃዎች ጠቁመዋል፡፡ የመከላከያ ሠራዊት አባላት በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ በወሰዱት የኃይል እርምጃ በጥይት ተመትተው የተገደሉ እና የቆሰሉ ነዋሪዎች መኖራቸው የተገለጸ ሲሆን፤ የተጎዱ ሰዎች ሐረር ወደሚገኙ የህክምና ጣቢያዎች መወሰዳቸውም ተነግሯል፡፡ የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ ኢሌ ከሶማሌ ክልል ጋር በሚዋሰነው የኦሮሚያ ክልል የድንበር አዋሳኝ ቦታ ላይ ጥቃት የፈጸሙት፣ ለክልሉ ልዩ ኃይል በሰጡት ትዕዛዝ መሠረት መሆኑን ነው መረጃዎች እያመለከቱ የሚገኙት፡፡
በሶማሌ ክልል እየተካሄደ ያለው ህዝባዊ ተቃውሞ እረፍት የነሳቸው አቶ አብዲ ኢሌ፤ በሁለቱ ክልሎች የድንበር አዋሳኝ ቦታዎች በሚኖሩ የኦሮሞ ተወላጆች ላይ አዲስ የማጥቃት ዘመቻ የፈጸሙት፤ በክልሉ በስፋት እየተቀጣጠለ ያለውን የተቃውሞ እንቅስቃሴ አቅጣጫ ለማስቀየስ እንደሆነ አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል፡፡ በኦሮሚያ ድንበር ጥቃት መፈጸሙ ያስቆጣቸው የምስራቅ ሐረርጌ ጭናቅሰን ነዋሪዎች፤ ድርጊቱን ለመቃወም ትላንት የአደባባይ ተቃውሞ ማካሄዳቸው የተገለጸ ሲሆን፤ መከላከያ ሠራዊት በነዋሪዎቹ ላይ የኃይል እርምጃ የወሰደውም በዚህ ወቅት መሆኑ ተነግሯል፡፡ እስካሁን ባለው መረጃ መሰረት፣ በተወሰደው የኃይል እርምጃ ሁለት ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፤ ለጊዜው ቁጥራቸው ያልታወቀ ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸው ታውቋል፡፡
የመከላከያ ሠራዊት አባላት በሰላማዊ ሰዎች ላይ የፈጸሙት ጭፍጨፋ የአካባቢውን ነዋሪዎች ማስቆጣቱን የሚገልጹት መረጃዎች፤ ድርጊቱም በአካባቢው ከፍተኛ ውጥረት መፍጠሩን መረጃዎቹ ያክላሉ፡፡ በጥይት ተመትተው ሆስፒታል የገቡ ሰዎች ሐረር በሚገኙ ሆስፒታሎች የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ቢታወቅም፤ የጤናቸው ሁኔታ ምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ለማረጋገጥ አልተቻለም ተብሏል፡፡ በመከላከያ ሠራዊት አባላቱ ከተገደሉ ሰዎች የአንዱ የቀብር ስነ ስርዓት መፈጸሙን ከመረጃዎች ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡
የሶማሌ ክልልን በርዕሰ መስተዳድርነት እየመሩ የሚገኙት አቶ አብዲ ኢሌ፤ በክልሉም ሆነ ከክልሉ ውጭ ባሉ ከተሞች ህዝባዊ ተቃውሞ እየተካሄደባቸው እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ ከሶማሌ ክልል ውጭ በድሬዳዋ ከተማ በየሳምንቱ አርብ ጸረ-አብዲ ኢሌ ተቃውሞ ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ ፕሬዚዳንቱ በሶማሌ ክልል የተነሳባቸውን ህዝባዊ ተቃውሞ አቅጣጫ ለማሳት ነው የተባለለትን ጥቃት በኦሮሚያ ክልል መፈጸማቸውን ተከትሎ ደግሞ፤ በትላንትናው ዕለት በምስራቅ ሐረርጌ ጭናቅሰን በተባለው አካባቢ ድርጊቱን በማውገዝ የተቃውሞ ሰልፍ ተካሂዷል፡፡ በዚሁ ሰልፍ ላይ በርካታ ነዋሪዎች አደባባይ ወጥተው አቶ አብዲ ኢሌን እና ያስፈጸሙትን ጥቃት ሲቃወሙ እንደነበር መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

source: BBN

No comments:

Post a Comment