Sunday, May 13, 2018

የአማራ ብሔርተኝነት ወግ በቤተ መንግሥት

የአማራ ብሔርተኝነት ወግ በቤተ መንግሥት

በአማራ ክልል ከሚገኙ ዞኖች የተጠሩ በርካታ ሰዎች ታድመዋል፡፡ ከአዲስ አበባም በጣት የሚቆጠሩ አማራዎችም ተገኝተዋል፡፡ አመሻሹ 11፡30 ላይ ከታችኛው ቤተ መንግሥት (ኢዮቤልዩ ቤተ መንግሥት) ተገኘን፡፡ 12፡00 ገደማ ላይ በቤተ መንግሥቱ የእንግዳ መቀበያ የተለያዩ መጠጦች ለሚፈልግ ሰው ይሰጡ ነበር፡፡ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ጃንሆይ (ዐጼ ኃይለ ሥላሴ) ግብር ከሚያበሉበት አዳራሽ ገብተን ታደምን፡፡
በጣት ከሚቆጠሩ ደቂቃዎች በኋላ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ (ዶ/ር አቢይ አህመድ)፣ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ (አቶ ደመቀ መኮንን)፣የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ( አቶ ብናልፍ አንዷለም)፣የክልሉ የኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ንጉሡ ጥላሁን ወደ መድረኩ መጡ፡፡
በመቀጠል አቶ ንግሡ ስለፕሮግራሙ በማስተዋወቅ እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ የምግቢያ ንግግር እንዲያደርጉ ጋበዟቸው፡፡
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የመግቢያ ንግግር በአጭሩ፤

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ አንድነት፣ ስለ ፍቅር፣ይቅር ስለመባባል ጠቀሜታና ፋይዳ ሰፋ ያለ ንግግር አደረጉ፡፡ በተለይ ስለይቅርታ ሁለት ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡ አንደኛው የደርግ ባለሥልጣናትን የሚመለከት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በውጭ አገር የሚገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ ነው፡፡
እንደ እሳቸው ገለጻ ወደ 23, 000 የሚደርስ ቁጥር ከቀይ ሽብር እና ደርግ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያን ጥሎ የተሰደደ ወይም በውጭ አገር የሚኖር ኢትዮጵያ አለ፡፡ ይቅር ተባብለን አገራቸው ገብተው በሰላም መኖር አለባቸው አሉ፡፡ የቀድሞው ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያምንም ይቀርታ አድርገንላቸው አገራቸው መጥተው መኖር አለባቸው አሉ፡፡
ስለ ሲኖዶሱ ሲናገሩም ፓትርያኩን አቡነ ማትያስን እንዳገኟቸውና ውጭ ስላለው ሲደኖዶስ እንዳወያይዋቸው፤ ሰላም ወርዶ አንድ ሆነው ጠንካራ ቤተ ክርስቲያን እንድትኖር ምኞታቸው እንደሆነ እንደገለጹላቸው ተናግረዋል፡፡
በመቀጠል በተለይ የብሔርተኝነትን ነገር ሲያነሱ ባልተቤታቸውን (ቀዳማዊት እመቤት ዝናሽን) ምሳሌ በማድረግ ጉዳዩን ማብራራት ቀጠሉ፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ በዚህ የእራት ግብዣ ላይ ቀዳማዊት እመቤቷ ታድመዋል፡፡ ሌሎች ግብዣዎች ላይ እንዳልተገኙ ገልጸው የዕለቱ ግብዣ ግን የአማራዎች እንደሆነ ሲነገራቸው እንደመጡ ተናገሩ፡፡ ይህንን ሲናገሩ እኛ አጨበጨብን፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን የሚያስጨበጭብ አይደለም አሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለፍቅር፣ስለአንድነት፣ስለይቅርባይነት በርካታ ቁምነገሮችን አካፈሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረው እንደጨረሱ አቶ ንጉሡ መድሩኩን እንዲመሩ ዲያቆን ዳንኤል ክብረትን ጋበዙ፡፡ ዳንኤልም መጠነኛ ንግግር አድረጎ ውይይቱን በመምራት ለተለያዩ ሰዎች ዕድል ሠጡ፡፡
የእለቱ ሁለት ዓይነት ታዳሚዎች፤
=============
ታዳሚ አንድ-ኢትዮጵያዊያኖቹ ብቻ
---------------
ያው እንደተለመደው በርካታ አባቶቻቸችን እና እናቶቻችን አማራ የሚታወቅበትን የኢትዮጵያዊነት ባህርይ አስተጋብተዋል፡፡ አንዳንድ ወጣቶችም በተመሳሳይ በዚሁ መንገድ ተጉዘዋል፡፡ ስለ ልማትና ተያያዥ ጉዳዮች አንስተዋል፡፡
ታዳሚ ሁለት-አማራየሆኑ ኢትዮጵያዊያኖቹ፤
---------------------------
በዚህ ምድብ ሥር የሚካተቱት ስለአማራ ብሔርተኝነት መንስኤውም ግቡም ከኢትዮጵያዊነት ጋር ስላለው ግንኙነትም አብራርተዋል፡፡ አስረድተዋል፡፡ የአማራ ብሔርተኝነት የተወለደው በበደል፣በመከፋት፣በመገፋት ነው፡፡ እንኳንስ ለኢትዮጵያ ለመላው ጥቁር ሕዝብ መኩሪያ በሆነው ታሪኩ እንዲያፍርበት ተሠራ፡፡ እምዬ ምኒልክን ያህል መሪ ስም መጥራት እንኳን እንዲያሸማቅቅ ተደረገ፡፡ አማራ አገር ቢያቀና ነፍጠኛ ተባለ፡፡ ኢትዮጵያዊ ነኝ ሲል ማን ኢትዮጵያዊ ያልሆነ አለ ተብሎ ትምክህተኛ ተባለ፡፡ በተለይ በሁለተኛው ሚኒሊየም (ከ1000-2000 ) በተካነወኑ የአማራ ታሪኮች አማራ እንዲያፍር ሌት ተቀን ተሠራ፡፡ ቀና እንዳይል በሚያሸቅቅ ሁኔታ ደባ እና በደል እተሠራበት፡፡ በመሆኑም ከታሪኩም ከባህሉም እንዲነጠል በተደራጀ መንገድ ተዘመተበት፡፡
ከኢኮኖሚውም እንዴት እንደተነጠ እና እንደተበደለ በርካታ ማነጻጸሪዎች እየቀረቡ አስተያየት ተሠጠ፡፡ ለአብነትም በኢትዮጵያ ካሉ ደረጃ አንድ ኮንትራክተሮች ውስጥ እንደው ስም ያለው አንድ ኮንትራክተር አለን? የሚል ጥያቄያዊ ትችት ቀረበ፡፡ ከኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን ከፖለቲካውም የደረሰበበትን መገለል ተነግሯል፡፡ በመሆኑም የአማራ ብሔርተኝነትን የፈጠረው ከ1983 ዓ.ም. በኋላ የደረሰበት በደል እንደሆነ በበርካታ ወንድምና እህቶች ተብራርቷል፡፡ (የአንዳንዶቹን ስም ያልገለጽኩት ያው በሚታወቅ ምክንያት ነው፡፡ )
የአማራ ብሔርተኝነት ለማንም ስጋት እንደማይሆን በተለይ ዶ/ር ሲሳይ መንግሥቴ አብራርተዋል፡፡ ሕወሃት ስትመሠረት ጠላት አብጅታ ነው፡፡ አማራን ጠላት አድረጋ፡፡ የአማራ ብሔርተኝነት ግን ማንንም በጠላትነት አልሳለም፡፡ ራሱን ለመከላከል እንጂ፡፡ (ነገሩ ያው የመክት ጉዳይ ነው!) አማራ መቼም ቢሆን መቼም በኢትዮጵያዊነት አይደራደርም፡፡ ነገር ግን አማራ ደግሞ ላይመለስ አማራ ሆኗል፤ አማራ ነው፡፡ በመሆኑም የአማራ ብሔርተኝነት ለማንም ስጋት እንዳልሆነ ተብራርቷል፡፡
አብሮ በመድረኩ የተነሳው አማራ ክልልም ሆነ ብአዴን፣ ጸረ አማራ ወይም አማራ ጠል ከሆኑ አማራሮች እንዲላቀቅ ነው፡፡ እነዚህ አማራን የሚጠሉ ጸረ አማራ አመራሮች አማራን በመምራትም ሆነ እንደ ጆፌ አሞራ ሌሎችን በመዞርና አማራን በማጥቃት መቀጠል እንደሌለባቸውም ተወስቷል፡፡
በተለይ ከየክልሉ የሚፈናቀሉ አማራዎች ጉዳይ በዚህ ምሽትም ትኩረት ተሰጥቶበታል፡፡ ብጹእ አባታችን አቡነ አብርሃም አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
የወሎ ቴሪሸሪኬር ሆስፒታልም ብዙ ሰው ከተናገረበት ጉዳይ አንዱ ነበር፡፡ ከከሚሴና አካባቢዋ የታደሙት አባቶች በአሸባሪነት ተከሰው ስለደረሰባቸው ግፍ ( ሽንት ሁሉ ይሸናባቸው እንደነበር) ሁሉንም ሰው ወደ ሐዘን ድባብ በከተተ ሁኔታ ተናግረዋል፡፡ ከሰሜን ወሎ የመጡ አንድ ጎልማሳም ስለወልዲያ፣ቆቦና መርሳ ሁኔታ ተናግረዋል፡፡ ሼክ አሊ አላሙዲንንም ለማስፈታት እንዲሞክሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመዝጊያ ንግግራቸው፤
===============
በታወቀው ንግግር አዋቂነታቸው እና በበርካታ ምሳሌዎች አሁንም ስለመተባበር፣ስለ አንድነት፣ ስለ ይቅር ባይነት በተለይም እምዬ ምኒልክን በምሳሌነት በማንሳት አስረድተዋል፡፡ የንጉሥ ተክለሃይማኖትና የእምዬን ታሪክ አውስተዋል፡፡ ማርከው የሚያክሙ እንዲሁም የሚሾሙ መሆናቸውን እና ይቅር ባይነታቸውን በአርያነት አንስተው አስረድተዋል፡፡
በመጋረጃ የተሸፋፈነውን የጃንሆይን ዙፋን አስከፍተው መኩሪያችን እንደሆነ፣ከመስከረም ጀምሮ ለሕዝብ ክፍት እንደሚሆን ሁሉ ተናገሩ፡፡ ላይኛው ቤተ መንግሥትንም (የምኒሊክ ቤተ መንግሥትንም)አስደናቂነት እና ሁላችንም የየድርሻችንን መወጣት እንዳለብን ተናግረዋል፡፡
የወሎ ቴሪሸሪ ኬር ሆስፒታልንም ከአቶ ደመቀ ጋር እንደተነጋገሩ እና ትኩረት እንደሚሰጡበት ተናግረዋል፡፡
የሼክ አሊ አላሙዲን ጉዳይንና ሌሎች በሳዑዲ አረቢያ የሚገኙ እሰረኞችን በሚመለከት ለመወያየት የፊተችን ሐሙስ ወደ ሳዑዲ እንደሚሔዱ ነግረውናል፡፡
ሦስት የመውጪያ ወጎች፤
========
አንድ
-----
አንዳንድ ሰዎች፣በዚሁ መድረክም ጭምር፣ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያዩ ቦታዎች መዟዟር እና መንቀሳቀስ ስላበዙ ጊዜ እንስጣቸው፤አሁን በየቦታው ቢዞሩም ቢሮ ሆነው ሥራ ባይሰሩም የሚል አንድምታ ያለው ንግግር ስለበዛ ይመስላል ጠቅላይ ሚኒስትሩ መደበኛ ሥራቸውን እና ውሳኔ የሚፈልጉ ጉዳዮችን እንደውም ከወትሮው በበለጠ ሁኔታ እየሠሩ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
ሁለት፤
------
ጠቅላዩ በዚሁ ግብር ላይም ጭምር እንደታየው ስለደረሰ በደል ስለተወራ እሳቸውም ብዙዎቻችን ተበድለናል አሉ፡፡ ለዚህም ደግሞ ፊታቸው ላይ የወጣውን ማድያት አሳዩን፡፡ ስለማዲያቱ ሁኔታ ይምታውቀው ባልተቤታቸው እንደሆነችም ተናገሩ፡፡
( ይቺን ነገር ለታዳሚው ከመናገራቸው በፊት በእራት ሰዓት እኔና ጓደኞቼ (ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው፣አንዷለም አባተ/የአጸዴ ልጅ፣ምንዳራለው ዘውዴ፣ዶ/ር ሰጥአርጋቸው) ወደተቀመጥንበት መጥው ስለነበር የእኔን እጅ ይዝው ፊታቸውን አሳዩኝ፡፡) ፊቴን ማድያት በማዲያት እንዲሆን ያደረጉትን ልበቀል ብል ስንት ሰው ማሰር አለብኝ? አሉ፡፡ በመበቃቀል ፍቅር አይገነባም አሉ፡፡
ሦስት፤
------
የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳድር የአቶ ገዱ አንዳርጋቸው ስም በብዙ ሰዎች በበጎ ተነስቷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም እንዲህ አሉ፡፡ ሰዎች ብዙ ጊዜ በአድናቆት የሚናገሩት ስለ አቶ ገዱና አቶ ለማ መገርሳ እንዲሁም አልፎ አልፎ ስለ እኔ ነው አሉ፡፡ ነገር ግን መርሳት የሌለባችሁ ከእኛ ጀርባ አንድ ሰው ያሉ መሆናቸውን ነው አሉ፡፡ እሳቸውም አቶ ደመቀ መኮንን ናቸው አሉ፡፡
በሉ ደህና እደሩ፡፡ ከምሽቱ 4፡30 አካባቢ ውይይቱ ተጠናቀቀ፡፡ እኔም ሌሊት ጻፍኩት፡፡ ለቴሌቪዥንም ይሁን ለሬዲዮ ቀረጻ አልተደረገም፡፡ ሞባይልም ካሜራም የለም፡፡"
(ውብሸት ሙላት)

No comments:

Post a Comment