በብርሃኑ ፈቃደና በዳዊት እንደሻው
የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን በደረጃ ‹‹ሐ›› ግብር ከፋዮች ላይ ባስቀመጠው አዲስ የታክስ ምጣኔ ሳቢያ በአዲስ አበባ ከተማ አራቱም ማዕዘናት ከፍተኛ እሮሮ እየተደመጠ ይገኛል፡፡ በርካቶች በቀን ገቢ ግምት ስሌት እንዲሁም በዓመታዊ ሽያጫቸው መሠረት የተጣለው ታክስ በየተጋነነ ነው በማለት፣ ቅሬታውን ለማቅረብ የክፍለ ከተማና የወረዳ ጽሕፈት ቤቶችን ሲያጨናንቁ ታይተዋል፡፡
ሰሞኑን በተፈጠረው በዚሁ የታክስ ግርግር ሳቢያ በርካታ ክስተቶች ተስተናግደዋል፡፡ በርካቶች ሲላቀሱ ታይተዋል፡፡ በየቀበሌው በድንጋጤ አቅላቸውን ስተው የሚዘረሩ ሰዎችም አልታጡም፡፡ ሪፖርተር በተጨባጭ ለማረጋገጥ ባይቻለውም በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 ውስጥ ነዋሪ የሆኑ ግለሰብ በቀን ግምት የሦስት ሺሕ ብር ታክስ ተጥሎባቸው ከድንጋጤ ብዛት መፀዳጃ ቤት ውስጥ ሞተው እንደተገኙ የአካባቢ ሰዎች ሲናገሩ የተመደጠ፣ የሰሞኑ የመነጋገሪያ ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ ሰንብቷል፡፡
ወ/ሮ ራሔል ስጦታው 24 ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በምግብ ንግድ ሥራ የምትተዳደር ስትሆን፣ አምስት ጠረጴዛዎችና 17 ወንበሮችን በምትይዘው ‹‹ቁርስ ቤቷ›› በቀን ከ15 እስከ 20 እንጀራ በመሸጥ ላለፉት ሦስት ዓመታት ስትሠራ እንደቆየች ለሪፖርተር ገልፃለች፡፡ ወ/ሮ ራሔል እንደጠቀሰችው፣ እነዚህን ዓመታት ከሰዎች በመደበር የጀመረችውን ሥራ ለማደራጀትና ቤተሰቧን ለማስተዳደር ስትጣጣር ቆይታለች፡፡ እስካሁንም ገንዘብ ላበደሯት ሰዎች ዕዳዋን ለመመለስ በምትሯሯጥበት ወቅት፣ የቤት ኪራይ ስለተጨመረባት የንግድ ፈቃዷን በመመለስ ምግብ ቤቷን ለመዝጋት እየተዘጋጅ ባለችበት ወቅት አዲሱ የታክስ ዱብ ዕዳ እንደመጣባት ትናገራለች፡፡ በወር ስምንት ሺሕ ብር ኪራይ የምትከፍልበት ንግድ ቤት፣ ወደ 15 ሺሕ ብር ብር ጨምሯል በመባሏ ነበር ሥራውን ለማቆም የወሰነችው፡፡
ወትሮውንም በወር ይህን ያህል የቤት ኪራይ እየከፈለች ስትሠራ የቆየችው የተበደረችውን ዕዳ መክፈል ግድ ስለሆነባት እንጂ፣ አቅሙ ኖሯት ሥራውን እንዳልገባችበት ገልፃለች፡፡ ከሰዎች 40 ሺሕ ብር ያህል ተበድራ፣ ሥራውን ስትጀምር የስድስት ወር ቅድሚያ ክፍያ መጠየቋ ነበር የመጀመሪያው ችግር፡፡ በብድር ካገኘችው ገንዘብ ላይ ቀናንሳ ብትከፍልም ሥራው የታሰበውን ያህል አልሆነም፡፡
በዚያም ላይ የኩላሊት በሽተኛ በመሆኗ እና እንደልቧ ጎንበስ ቀና ብላ መሥራት ባለመቻሏ፣ ሥራውን በአግባቡ ለማስኬድ መቸገሯን ጠቅሳለች፡፡ እንዲህ እየተፈተነች ባለችበት ወቅት፣ በዓመት 49 ሺሕ ብር የታክስ ዕዳ ሲመጣባት የምትጨብጠው፣ የምትይዝ የምትሆነው እንዳጣች እንባዋን እያዘራች ገልጻለች፡፡ በየዓመቱ 5,700 ብር ያህል ስትከፍል ብትቆይም ይህም ቢሆን ከአቅሟ በላይ ሆኖባት ስትፍጨረጨር መቆየቷን አስታውሳ፣ አዲስ የተጠየቀችውን የምትከፍልበት የሥራ እንቅስቃሴ እንደሌለ በመግለጽ አቤቱታ ማስገባቷንም ገልጻለች፡፡
‹‹እኔ ይህንን ያህል መክፈል አልችልም፡፡ ተቀጥሬም ሆነ እንደሌሎች ጓደኞቼ ስደት ሄጄ መሥራት አልችልም፡፡ በሽተኛ ነኝ ስላቸው እጄን ይዘው አስወጡኝ፡፡ የሚሰማን ሰው የለም፡፡ አታፍሪም ብትችይ አይደል እንዴ ይህን ያህል ጊዜ ስትሠሪ የቆየሽው? ካልቻልሽ ለምን በስድስት ወር ውስጥ አትዘጊውም ነበር፤›› እንዳሏት እሷም ‹‹ነገ የተሻለ እሠራለሁ በማለት የተሸጠው ተሽጦ የተረፈውን በልቼ ማደሬን እንጂ ትርፍ እስካሁን አላገኘሁም፡፡ እስካሁን የተሳካልኝ ነገር ቢኖር የነበረብኝን ብድር መመለስ መቻሌ ነው፤›› ያለችው ራሔል፣ ኑሮ ይባስ እየተወደደ፣ በመጣበት ወቅት ሁለት መንታ ልጆቿን ጨምሮ እናትና አባት የሌላቸው እህት ወንድሞቿን ለማስተዳደር ቀና ደፋ በምትልበት ወቅት እንዲህ ያለው ጉድ ያውም ከመንግሥት መምጣቱ ቅስሟን ከመስበር አልፎ፣ በሕይወት ተስፋ እንዳይኖራት ማድረጉን ጠቅሳለች፡፡
እንዲህ ያሉ ታሪኮች የተደመጡበት የዚህ ዓመት የታክስ ጉዳይ የሁሉም ሰው መነጋገሪያ ሆኖ ቀጥሏል፡፡ በርካቶች በመንግሥት ላይ ብሶታቸውን እያሰሙ ይገኛሉ፡፡ ከስድስት ዓመታት በፊትም እንዲሁ ተመሳሳይ ቅሬታዎች በመንግሥት ላይ ሲሰነዘሩ እንደነበር ይታወሳል፡፡ የአሁኑን ይበልጥ አሳሳቢ ያደረገው ግን መንግሥት ባሻሻለው የታክስ ምጣኔ መሠረት ከታችኛው ክፍል ወደ ላይ መሔድ የሚገባቸው በርካታ ግብር ከፋዮችን ለማግኘት በማሰብ፣ የታክስ መሠረቱን የማስፋት ዕርምጃው አካል እንደሆነ አስታውቋል፡፡
በመሆኑም የደረጃ ‹‹ሐ›› ግብር ከፋዮች ዓመታዊ የሽያጭ መጠን እስከ 500 ሺሕ ብር እንዲሆን በመደረጉ፣ በዚህ መደብ ውስጥ የሚገቡት ነጋዴዎች ምንም እንኳ የገቢ መጠናቸው ዝቅተኛ ነው ቢባልም መክፈል የሚገባቸው የታክስ መጠን ላይ የተደረገው ማሻሻያ ግን ከአቅማቸው በላይ መሆኑን በምሬት እያስተጋቡ ይገኛሉ፡፡
ሪፖርተር ስለዚሁ ጉዳይ ተዘዋውሮ መረጃ ካጠናቀረባቸው አካባቢዎች መካከል አንዱ ቦሌ ቡልቡላ ነው፡፡ በዚህ አካባቢ የሚገኙ አነስተኛ ነጋዴዎችም እንደሌሎቹ አካባቢዎች ሁሉ ‹‹ታክስ አንፈልም አላለንም፡፡ ለዓመታት ስንከፈል ኖረናል፡፡ የአሁኑ ግን ከሚታሰበው በላይ ቅጥ ያጣና ከምናገኘው ገቢ ጋር ፈጽሞ የማይመጣጠን ነው፤›› ያሉት በቦሌ ቡልቡላ በአነስተኛ መደብር ውስጥ ነጠላ ጫማና ሌሎችም የፕላስቲክ ውጤቶችን የሚሸጡት አቶ አበራ ተሰማ ናቸው፡፡ አቶ አበራም ሆኑ በርካታ የእሳቸው ብጤ ነጋዴዎች የጋራ ቋንቋቸው የተጣለው የገቢ ግምት የአካባቢውን እንቅስቃሴ ከግምት ውስጥ ያላስገባ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ በዓመት 450 ብር ሲከፍሉ የነበረው የታክስ መጠን በአዲሱ ተመን መሠረት ከፍተኛ ጭማሪ እንዲኖረው በመደረጉ ተማረዋል፡፡
ጌሾና ብቅል የሚሸጡ፣ ጉልት የሚቸረችሩ፣ የ‹‹አርከበ ሱቅ›› በሚባሉት አነስተኛ መደብሮች ልዩ ልዩ ሸቀጦችን የሚነግዱ በጠቅላላው የታክስ ግመታው ከተጣለባቸው ከ150 ሺሕ የሚጠጉ ነጋዴዎች ውስጥ አብዛኛው በመንግሥት ላይ እሮሮውን እያሰማ፣ በየወረዳው ማመልከቻ ለመስገባት ሲጣደፉ ታይተዋል፡፡ ሆኖም አብዛኞቹ ከሦስት ወር በፊት ምላሽ እንደማያገኙ እየተነገራቸው፣ ጥቂት የማይባሉትም በአግባቡ የሚያስረዳቸው በማጣት መንገላታታቸውን ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡
የምሁራን ምልከታ
መንግሥት አብዛኛው ከታክስ መረብ ውጭ የሆነውን ነጋዴ ብቻም ሳይሆን፣ በታክስ ሥርዓቱ ውስጥ ተካቶም ተገቢውን ታክስ አልከፈለም ብሎ ባሰበው ክፍል ላይ የተከተለው አካሔድ ከግልጽነት ጀምሮ የአተገባበር ወጣ ገባነት እንደሚታይበት ሲገለጽ ይታያል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ሕዝቡ እንዲዘጋጅበት የሚመጣው የታክስ ምጣኔ ድንገተኛ ከሚሆን ይልቅ ወቅቱን በጠበቀ መልኩ ካለው የኑሮ ውድነት ጋር እየተገናዘበ የሚጣል መሆን ሲገባው፣ በአንድ ጊዜ ያውም ከስድስት ዓመታት ቆይታ በኋላ እንዲህ ከፍተኛ ጭማሪ አስከትሎ መምጣቱ ተቀባይነት እንደሌለው ከሚገልጹት ባለሙያዎች መካከል አንዱ ዶ/ር ታደሰ ሌንጮ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ታክስ ሥርዓት ውስጥ የዳበረ ልምድ ያላቸው ዶ/ር ታደሰ በኢትዮጵያ የታክስ ግመታ የሚካሔደበትን ሥርዓትና የሚጣለውን የግምት ታክስ መጠን ኮንነዋል፡፡
እንዲህ ያለው ሒደት በአንድ ጀምበር እንደማይከናወን፣ ይልቁንም የታክስ ግምቱ ከመቀመጡ በፊት ሰፊ የማጣራት ሥራዎች መከናወን እንደነበረባቸው አብራርተዋል፡፡ ለታክስ ግመታው የሚረዱ ሳይንሳዊ ዘዴዎች ቢተገበሩ ኑሮ የስህተት ደረጃውን ሊቀንሱት ይችሉ እንደነበር በመግለጽ፣ የታክስ ግመታው ከመደረጉ ቀደም ብሎም ከነጋዴው ማኅበሰረብ ጋር በመነጋገርና መግባባት ላይ በመድረስ ለግምት ስለሚጠቀምባቸው ዘዴዎችና የአተማመን ሒደቶች አመላካች ነጥቦችን ማብራራት ይጠበቅበት እንደነበርም ጠቅሰዋል፡፡ ‹‹በትክክል ሠርተውት ቢሆን ኑሮ ይህ ሁሉ ሰው አይቃወማቸውም ነበር፤›› ብለዋል፡፡ ይልቁንም የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋናው ዓላማ የታክስ ገቢውን ማሳደግ ብቻ እንዳስመሰለውም ከመግለጽ አልተቆጠቡም፡፡ በመሆኑም የተከተሉት የትመና ሥርዓት ሳይንሳዊ እስካልሆነ ድረስ፣ የሕዝቡም ተቃውሞ እስከቀጠለ ድረስ ፖለቲካዊ ሚና ሊኖረው እንደሚችልም አሳስበዋል፡፡ በመሆኑም የታክስ አስተዳደሩ ባለሥልጣናት ከበላይ ስልክ ተደውሎላቸው ተዉ ሊባሉ እንደሚችሉም ከሚታየው የሕዝቡ ቅሬታና ተቃውሞ በመነሳት ግምታቸውን በማስቀመጥ መንግሥት የተመነውን የታክስ መጠን ሊያነሳ እንደሚችል ጠቅሰዋል፡፡
የተቃማዊ ፓርቲዎች መግለጫ
ሆኖም ሰሞኑን መግለጫ የሰጡት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የታክስ ፕሮግራም ምክትል ዳይሬክተር ወ/ሮ ነፃነት አበራ፣ ሰዎች ቅሬታ ካላቸው በተናጠል እንደሚስተናገዱ ተናግረዋል፡፡ በቡድን ለሚቀርብ የትኛውም ዓይነት ጥያቄ ምላሽ እንደማይሰጥ የጠቀሱት ወ/ሮ ነፃነት፣ ታክስ ከፋዮችን በተናጠል በመገምገም የታክስ ግምቱ እንደተጣለባቸው በማስታወቅ የሚቀርብ ቅሬታ ካለም በዚሁ አግባብ ብቻ እንደሚስተናገድ ገልጸዋል፡፡
እሳቸው ይህን ይበሉ እንጂ በተናጠልም ቢሆን የሚቀርበው ቅሬታ ተገቢውን ምላሽ እንደማያገኝ ታክስ ከፋዮች እየተናገሩ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር አሁን ታክስ ከፋዮቹ አሁን የተጠየቁት የታክስ መጠን ሙሉውን እንዳልሆነና በመጪው በጀት ዓመት ሙሉውን መጠን መክፈል እንደሚጠበቅባቸው እየተነገራቸው በመሆኑ፣ ቅሬታቸውን እያባባሰው እንደሚገኝ ሲገልጹ ይደመጣል፡፡
የሰሞኑን የታክስ ግርግር በመንተራስ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) እና ሰማያዊ ፓርቲ (ሰማያዊ) ሰኔ 29 ቀን 2009 ዓ.ም. ባወጡት መግለጫ፣ ‹‹በአዲስ አበባ ነጋዴዎች ላይ የተተመነው ከአቅም በላይ የሆነ የግብር ዕዳ እንዲሻሻል አጥብቀን እንጠይቃለን፤›› ብለዋል፡፡ በፓርቲዎቹ መግለጫ መሠረት ይህ የግብር ዕዳ ዜጎች በአገራቸው ነግደው ለማደር ያላቸውን ተስፋ የሚያሟጥጥና ለስደት የሚዳርግ ከመሆኑም በላይ በስደት የሚገኙ ወገኖችም ወደ አገር ቤት ለመመለስ ፈቃደኛ እንዳይሆኑ ከሚያደርጉ ምክንያቶች መካከል ዋነኛው እንደሚሆን እና መንግሥትም ልብ ሊለው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በተጣለባቸው ከፍተኛ የግብር ጫና ምክንያት የንግድ ፈቃድ ለመመለስና ከሥራ ለመውጣት የጠየቁ ነጋዴዎች እስከ ጥቅምት ወር 2010 ዓ.ም. ድረስ መመለስ እንዳይችሉ መከልከላቸውን ፓርቲዎቹ ተቃውመው፣ መመለስ ቢችሉ እንኳ ሥራ ካቆሙበት ጊዜ ጀምሮ ንግድ ፈቃዳቸውን እስከመለሱበት ጊዜ ድረስ ያለውን የገቢ ግብር በአዲሱ ተመን መሠረት መክፈል እንዳለባቸው መቀመጡንም ኮንነዋል፡፡ በመሆኑም መኢአድና ሰማያዊ የመንግሥትን ድርጊት በማውገዝ ባለአራት ነጥብ የአቋም መግለጫውን ይፋ አድርገዋል፡፡
ምንም እንኳ ነጋዴዎቹም ሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ምሁራንም ጭምር የመንግሥትን የግምት ታክስ አሠራር ቢቃወሙም፣ መንግሥት ግን ሊከፈለው የሚገባ በርካታ ገንዘብ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ሰኔ 30 ቀን 2009 ዓ.ም. በፓርላማ መዝጊያ ንግግራቸው፣ ይህ የታክስ አሠራር እንደሚቀጥል ቆፍጠን ባለመንገድ አስታውቀዋል፡፡
በሚቀጥለው በጀት ዓመት መንግሥት ከከተማው ታክስ ከፋዮች እንደሚሰበስብ ያስታወቀው የታክስ መጠን 26 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ ባለፈው በጀት ዓመት ባለሥልጣኑ የሰበሰበው መጠን 129.6 ቢሊን ብር ሲሆን ከዕቅዱ የ18 ቢሊን ብር ያህል ቅናሽ ያሳየ መጠን እንደሆነም አስታውቋል፡፡ አብዛኛውን አገሪቱን የልማት ወጪዎች በራስ አቅም ለመሸፈን ባለው አቋም መሠረት 80 በመቶ ያህል ወጪዎቹን በዚሁ አግባብ ከአገር ውስጥ ምንጮች ለመሸን እንደቻለም ሲገልጽ ይደመጣል፡፡ ይሁንና አሁንም ድረስ በታክስ መረብ ውስጥ ያልተካተተ ሰፊ የንግድ ማኅበሰረብ እንደሚገኝ ሲገልጽ ዋናው መደበቂያ ደግሞ የደረጃ ‹‹ሐ›› ግብር ከፋዮች ውስጥ የሚገኙት እንደሆኑ አስታውቋል፡፡ ከዘጠኝ ሺሕ ያላነሱ ነገር ግን ከፍተኛ ግብር ከፋይ መሆን የሚገባቸው ነጋዴዎች እንደሚገኙ መንግሥት ያምናል፡፡
በሌላ በኩል ከተቀጣሪዎች የሚሰበሰበው የታክስ መጠን ከፍተኛ የመሆኑን ያህል ከነጋዴው የሚገኘው ከሚጠበቀው ይልቅ አነስተኛ መሆኑ ብቻም ሳይሆን አብዛኛው ኅብረሰተብ ታክስ የመክፈል ልማድ ባለማዳበሩ ችግሮች እንደሚከሰቱ ይገልጻል፡፡ ምንም እንኳ መንግሥት በግምት የሚጣለውን የታክስ ሥርዓት እንደማያምንበት ከዚህ ቀደም ቢያስታውቅም፣ አማራጭ ስሌለው ግን ይህንኑ መንገድ እንደተከተለም ይጠቅሳል፡፡
ይህም ሆኖ ባለሥልጣኑ ታክስ ከፋዩ ‹‹ባመነው ልክ ይክፈል፤›› የሚል አሠራር እንደሚከተል በዚሁ አግባብም ታክስ እንደሚያስከፍል ቢናገርም፣ በተግባር ግን ልምድ የሌላቸው ገማቾችን በየመደብሩ በማሰማራት ግምት ማውጣቱ ሲኮነን ቆይቷል፡፡ ከስድስት ዓመታት በፊት እንደተደረገው ዘንድሮም ተመሳሳዩ አካሔድ የተተገበረ ሲሆን፣ የዘንድሮው ግን ሁለት ጊዜ እንደተካሔደ ይታወቃል፡፡ በመጀመሪያው ዙር የተደረገው ግመታ ተቀባይነት በማጣቱ በድጋሚ እንዲገመት የተደረገበት አግባብም በአብዛኛው ነጋዴ እሮሮ እንዲነሳበት ምክንያት ሆኗል፡፡ Read more here
No comments:
Post a Comment