Monday, July 10, 2017

ጥቂት ዕውነቶች ስለጣና ሐይቅ፤

Captureq
ጥቂት ዕውነቶች ስለጣና ሐይቅ፤

1. ከ10% እስከ 15% ወይም ከሦስት ሚሊዮን በላይ የሚሆነው የዐማራ ሕዝብ ኑሮው የተመሠረተው በጣና ሐይቅ ላይ ነው፡፡ የባሕር ዳር ከተማን ጨምሮ በምዕራብ ጎጃም፣ በደቡብና በሰሜን ጎንደር ዞኖች የሚገኙ 54 ቀበሌ ገበሬ ማኅበራት ኢኮኖሚያዊ መሠረታቸው ከጣና ሐይቅ በሚገኝ የአሣ ምርትና መስኖ ነው፡፡ 
2. የኢትዮጵያን 50% የንጹህ ውኃ ክምችት የያዘ ጣና ነው፡፡ 
3. ከ40 በላይ ወንዞችና ጅረቶች ወደ ጣና ሐይቅ ይፈሳሉ፤ የዓለማችን በርዝመቱ ትልቁ ወንዝ ዓባይ ከጣና ሐይቅ ይነሳል፡፡ ወደ ሐይቁ ከሚገቡ ወንዞችና ጅረቶች መካከል ግልገል ዓባይ፣ ርብ፣ ጉማራ፣ እንፍራንዝና መገጭ ይገኙበታል፡፡
4. በጣና ሐይቅ ውስጥ ከ31 በላይ ደሴቶች አሉ፡፡ ትልቁ ደሴት የደቅ ደሴት ሲሆን 16 ካሬ ኪሎ ሜትር አለው፤ 4,816 ሰዎች በደሴቱ ላይ ይኖራሉ፡፡ ደሴቶቹ በጥንታዊ ገዳማትና ታሪክ የታጨቁ ናቸው፡፡ ረዥም እድሜ ያለው ገዳም የጣና ቂርቆስ ሲሆን በብሉይ ዘመን የኦሪት መስዋት ሲሰዋባቸው ከነበሩት ቦታዎች አንዱ ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድ እንደ አንቀጸ ብርሃን፣ ዚቅና የዜማ ድርሰቶች የደረሰው በዚሁ ደሴት ገድሞ ነው፡፡
5. የጣና ሐይቅ በትንሹ 19 ዓይነት ገበሎ አስተኔዎች፣ 35 ዓይነት ተሳቢዎች፣ 28 ዓይነት አጥቢዎችንና 437 ዓይነት የተለያዩ አእዋፋትን የያዘ ነው፡፡
6. የጣና ሐይቅ ምድቡ በከፍተኛ ቦታዎች ላይ የሚገኝ ሲሆን ከባሕር ወለል በላይ 1800 ሜትር ከፍ ያለ ነው፡፡
7. ሐይቁ 90 ኪሎ ሜትር የዲያሜትር ርዝመትና የ385 ኪሎ ሜትር የጠርዝ ርዝመት አለው፡፡ የሐይቁ ጥልቀት ከ4 እስከ 14 ሜትር ጥልቀት ሲኖረው አማካይ ጥልቀቱ 8 ሜትር አካባቢ ነው፡፡ ቀደም ሲል 9.8 ሜትር አማካይ ጥልቀት እንደነበረው ይገመታል፡፡
8. የሐይቁ ስፋት 3672 ካሬ ኪሎ ሜትር የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ 3000 ብቻ ቀርቷል፡፡ 672 ካሬ ኪሎ ሜትር የሚሆነው ውኃ ደርቋል ወይም ወደ የብስነት ተቀይሯል፡፡
9. የጣና ሐይቅን አደጋ ላይ የጣሉ አራት ምክንያቶች እስካሁን በውል ተለይተው ታውቀዋል፡፡ እንደጥፋት መጠናቸው ቅደም ተከተል የጣና በለስ ኃይል ማመንጫ፣ የእንቦጭ አረም፣ የከተሞች ፍሳሽና በደለል መሞላት ናቸው፡፡ የጣና በለስ ኃይል ማመንጫ ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ የሐይቁ ጥልቀት ከ50 ሣ.ሜ በላይ ጥልቀት ቀንሷል፡፡ ከጎንደርና ከባሕር ዳር ከተማዎች የሚወጣ ወደ ሐይቁ የሚለቀቅ ቆሻሻ ሐይቁን እየበከሉት ነው፡፡
10. ከእምቦጭ አረም ውጭ ሌሎች ሁለት የተለያዩ መጥፎ አረሞች ጣናን እንደወረሩት ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ እንቦጭ በጣና ላይ የተከሠተው በፈረንጆች አቆጣጠር በ2011 ሲሆን እንቦጭ ቆቃን ጨምሮ በሌሎች የኢትዮጵያ ሐይቆች ውስጥ እንደነበረ ጥናቶች ጠቁመዋል፡፡
11. በ2014 እና 15 በጣና ሐይቅ ላይ በእንቦጭ ተሸፍኖ የነበረው የጣና ክፍል 20 ሺህ ሔክታር ቢሆንም በ2017 ወደ 24 ሺህ ሔክታር ከፍ ብሏል፡፡
12. እምቦጭ 50 በመቶ የሚሆነውን የሐይቁን ጠርዝ ወሮታል፡፡ እምቦጭ ወደ ጣና የገባው በመገጭ ወንዝ ጫፍ አካባቢ እንደሆነ ሲገመት በፎገራ በኩል ከሩዝ ምርት ጋር ሌሎች ሁለት መጥፎ አረሞች እንደገቡ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡ ሁለቱ ሌሎች መጤ አረሞች Azolla እና water lettuce በመባል ይታወቃሉ፡፡ Read from the source here

No comments:

Post a Comment