Monday, February 20, 2017

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በእንጦጦ ተራራ በ4.8 ቢሊዮን ብር የቱሪስት ማዕከል ለመገንባት ተዘጋጀ

Image result for addis ababa entoto national park
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ4.8 ቢሊዮን ብር ካፒታል በእንጦጦ ተራራ ላይ ደረጃውን የጠበቀ የቱሪስት ማዕከል ለመገንባት ዕቅድ ነደፈ፡፡
በሰሜን አዲስ አበባ በሚገኘው እንጦጦ ተራራ በ4,200 ሔክታር ቦታ ላይ የሚያርፈውን የቱሪስት ማዕከል ግንባታ ለማስጀመር በከንቲባ ድሪባ ኩማ የሚመራ ሥራ አመራር ቦርድ ተሰይሟል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤትና ማዕከሉን ማቋቋም የሚያስችሉ የሕግ ማዕቀፎች ተዘጋጅተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ገብረ ጻዲቅ ሐጎስ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የቱሪስት ማዕከሉ አራት ማዕቀፎች አሉት፡፡
ከእነዚህ ማዕቀፎች ውስጥ የመጀመሪያው የብሔርና ብሔረሰቦች ማዕከል ግንባታ ነው፡፡
አዲስ አበባ የብሔርና የብሔረሰቦች ከተማ ብትሆንም፣ የብሔሮችና ብሔረሰቦች ማዕከል የላትም ያሉት የቢሮ ኃላፊው፣ ‹‹ማንኛውም ዓይነት ቱሪስት አዲስ አበባ ቢገባ የሚገነባውን የባህል ማዕከል በመጐብኘት ኢትዮጵያን መመልከት እንዲችል ማድረግ ይቻላል፡፡ በዚህም አንድ ቱሪስት ስለኢትዮጵያ ሙሉ መረጃ እንዲኖረው ያደርጋል፤›› ሲሉ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
ሁለተኛው ማዕቀፍ የመዝናኛ ማዕከላት ግንባታ ነው፡፡ በዚህ ፕሮጀክት ሎጆችና አምስት መቶ ሜትር ርዝመት ያለው ማማ (ታወር) ይገነባል፡፡ ማማው የተለያዩ ሬስቶራንቶችን ከመያዙ በተጨማሪ እየተሽከረከረ ከተማውን ማሳየት ያስችላል ብለዋል፡፡
‹‹በዕረፍት ቀናት የከተማው ነዋሪዎች ከአዲስ አበባ ወጥተው ይዝናናሉ፣ እዚሁ እንዲዝናኑ አማራጭ ሊፈጠር ይገባል፡፡ የቱሪስቶች የመቆያ ጊዜም እንዲጨምር ያደርጋል፤›› ሲሉ አቶ ገብረ ጻዲቅ የመዝናኛ ማዕከላት መገንባት ያለውን ጠቀሜታ ገልጸዋል፡፡
ሦስተኛው ማዕቀፍ እንጦጦን የአትሌቶች የመለማመጃ ማዕከል ማድረግ ነው፡፡ እንጦጦ ያለው የአየር ፀባይ ለአትሌቲክስ ስፖርት የተመቸ በመሆኑ፣ የአገር ውስጥና የሌሎች አገሮች አትሌቶች ጥያቄ ሲያቀርቡ መቆየታቸው ተገልጿል፡፡
‹‹ጉዳዩ በመታመኑ የአትሌቲክስ ስፖርት የልምምድ ማዕከል ግንባታ ይካሄዳል፤›› ሲሉ አቶ ገብረ ጻድቅ ተናግረዋል፡፡ አራተኛው ማዕቀፍ ደግሞ የኢትዮጵያ ብሔርና ብሔረሰቦች የራሳቸውን ሙዚቃ፣ ወግ፣ ሥርዓትና ባህል ለታዳሚዎች በቀጥታ የሚያቀርቡባቸው ግንባታዎች ይካተታሉ፡፡
ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት ወደ ተግባር ከመለወጡ በፊት የከተማው አስተዳደርና ሕዝቡ የሚመክርባቸው መድረኮች ይዘጋጃሉ ተብሏል፡፡
የእዚህን ፕሮጀክት አዋጪነት ጥናት የዓለም ባንክ ፋይናንስ አድርጎ ያስጠናው በመሆኑ፣ ግንባታውንም የዓለም ባንክ ፋይናንስ እንዲያደርገው ንግግር እየተደረገ መሆኑን ከንቲባ ድሪባ ኩማ ገልጸዋል፡፡ ይህንን አዲስና ግዙፍ ግንባታ ለማካሄድ የአምስት ዓመታት ስትራቴጂካዊ ዕቅድ መነደፉ ታውቋል፡፡   Read more here

No comments:

Post a Comment