Monday, December 5, 2016

‹‹የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የሚፈለገውን ግብ እስከመታ ድረስ የግድ ስድስት ወራት የሚቆይበት ምክንያት የለም››

የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር
መንግሥት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመጠበቅና ሰላም ለማስፈን በመላ አገሪቱ ተግባራዊ እንዲሆን የደነገገው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለስድስት ወራት ላይቆይ እንደሚችል፣ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትሩ ፍንጭ ሰጡ፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ከመስከረም 28 ቀን 2008 ዓ.ም. አንስቶ ለስድስት ወራት ቆይታ የተጣለ መሆኑ ይታወቃል፡፡
አዋጁ ተግባራዊ ሲደረግ በቆየባቸው ሁለት ወራት ገደማ የአገሪቱን ሰላምና መረጋጋት ወደ ቀድሞ ሁኔታ መመለስ መቻሉን ሚኒስትሩ ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ ተናግረዋል፡፡ ‹‹የአስቸኳይ አዋጁ የሚፈለገውን ግብ እስከመታ ድረስ የግድ ስድስት ወራት የሚቆይበት ምክንያት የለም፤›› ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በቅርቡ ተቀማጭነታቸው በአዲስ አበባ ከሆነ ዲፕሎማቶች ጋር በተወያዩበት ወቅትም ይህንኑ እንዳስረዱ ገልጸዋል፡፡
‹‹ስለዚህ መንግሥት ይህንን በሒደት አይቶ ዕርምጃ የሚወስድበት ሁኔታ እንደሚኖር መገንዘብ ያስፈልጋል፤›› ብለዋል፡፡
ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ውስጥ እንዲቀሩ ወይም እንዲሻሻሉ የሚገባቸውን ድንጋጌዎች አስመልክቶ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚያስፈጽመው ኮማንድ ፖስት መግለጫ እየሰጠ መሆኑን ያስታወሱት ሚኒስትሩ፣ ሰሞኑንም ኮማንድ ፖስቱ መግለጫ ለመስጠት ዝግጅት ላይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ይሁን እንጂ በመግለጫው ይዘት ላይ ያሉት ነገር የለም፡፡ ‹‹ግምገማዎች እየተካሄዱ ነው፣ ጊዜውን ጠብቀን የምንሰማው ይሆናል፤›› ብለዋል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ተከትሎ ኢንተርኔት በኢትዮጵያ እንዲዘጋ ተደርጓል በሚል የሚናፈሰው መረጃ አሉባልታ መሆኑን የተገለጹት ዶ/ር ነገሪ፣ ‹‹የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አካል የሆነው የሞባይል ኢንተርኔት ነው፤›› ብለዋል፡፡
የሞባይል ኢንተርኔት ላይም ግምገማ ተካሂዶ ሊለቀቅ የሚችልበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡    Read more here

No comments:

Post a Comment