Monday, November 7, 2016

የቅንጅት አመራሮች ሊቀመንበሩን አማረሩ

‹‹ድርጅቱን እንደግል ንብረት ይጠቀሙበታል››
   የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ አመራሮች፤ የድርጅቱን ሊቀመንበር አየለ ጫሚሶን አማረሩ፡፡ አመራሮቹ ለአዲስ አድማስ እንደገለፁት፤ሊቀመንበሩ መንግስት ለድርጅቱ መጠቀሚያነት የሰጠውን ቤት ከፋፍለው በማከራየት፤ በወር እስከ 17 ሺህ ብር ለግላቸው ገቢ የሚያደርጉ ሲሆን አመራሮቹ ቢሮ በማጣት በየካፌው ለመሰብሰብና ለመወያየት መገደዳቸውን ተናግረዋል፡፡

‹‹አቶ አየለ ጫሚሶ አምባገነናዊ አካሄድ በመከተል፣ ከፓርቲው መተዳደሪያ ህግና ደንብ ውጭ እየሄዱ ነው›› ያሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ‹‹ይህን ለምን ታደርጋለህ?›› በሚል የጠየቃቸውን ሁሉ ‹‹ታግደሀል›› በማለት ከተሰጣቸው ስልጣን ውጭ አመራሮችን ያግዳሉ ብለዋል፡፡ የኦዲትና ኢንስፔክሽን ቢሮውን ዘግተው፤ ሀላፊዎቹን ማገዳቸውንም፤ የድርጅቱ የወጣቶችና የማህበራዊ ጉዳይ ሀላፊ፤ አቶ አስረስ በትረ ተናግረዋል፡፡ 
‹‹አቶ አየለ የፓርቲውን መተዳደሪያና ውስጠ ደንብ ጥሰው ስለመንቀሳቀሳቸው በርካታ ማስረጃዎች አሉ›› ያሉት አቶ አስረስ፤ ጠቅላላ ጉባኤ ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር መጠራት ሲገባው እስካሁን አለመጥራታቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡ 

 ይህንን ጉዳይ እርሳቸውም ሆነ የኦዲትና ምርመራ ሀላፊዎች ለምርጫ ቦርድ ማመልከታቸውን የተናገሩ አቶ አስረስ ቦርዱ “ስብሰባውን እንዲጠራ መልዕክት አስተላልፋለሁ፤” ከማለት ውጭ የወሰደው እርምጃ የለም ብለዋል፡፡ ‹‹እስካሁን በጠቅላላ ጉባዔው ተመርጠው 
በአመራርነት ላይ ከሚገኙት ውስጥ እኔና ሊቀመንበሩ ቀርተናል›› ያሉት አቶ አስረስ፤ ሌሎቹን በማገድና በማባረር ሊቀመንበሩ የሚፈልጓቸውን ሰዎች እያመጡ አስቀምጠዋል ብለዋል፡፡ 

የድርጅቱ የኦዲት ፀሀፊ አቶ ዳንኤል ታደሰ በበኩላቸው፤ ‹‹የምንሰራባቸው ቢሮዎች ተከራይተዋል፤ አመራሮች ቅሬታቸውን ለሊቀመንበሩ በቢሯቸው ቢያቀርቡም ጥያቄውን ላለመቀበል ሊቀመንበሩ በላያቸው ላይ መስኮት ዘግተው ጥለዋቸው ወጥተዋል፡፡ ‹‹አቶ አየለ በጣም አምባገነን ናቸው›› ያሉት አቶ ዳንኤል፤ እሳቸውን  ተቃውሞ ሀሳብ ያነሳ ሁሉ ይባረራል፤ ይታገዳል ብለዋል፡፡ 
የኦዲትና ምርመራ ሶስት ሀላፊዎች ተፈራርመው ችግሩን ለምርጫ ቦርድ ቢያቀርቡም፣ ‹‹ቲተር የላችሁም›› በሚል እንደመለሷቸው የሚናገሩት አቶ ዳንኤል፤ ‹‹ሊቀመንበሩ ግን ያለ ማህተም ከምርጫ ቦርድ ጋር ደብዳቤ ሲለዋወጡ ተመልክተናል፤ እኛ የምንፈልገው ጠቅላላ ጉባኤ ተጠርቶ ሁሉም ነገር በግልፅ እንዲወጣና የፓርቲው አሰራር እንዲጠራ ነው ብለዋል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ ማብራሪያ የጠየቅናቸው የድርጅቱ ሊቀመንበር አቶ አየለ ጫሚሶ በበኩላቸው ጉዳዩ በፍ/ቤት ስለተያዘ አስተያየት ከመስጠት እንደሚቆጠቡ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡ Read more here

No comments:

Post a Comment