Monday, November 28, 2016

‹‹ጭላንጭል ብርሃን ቢታየኝም እዛ ለመድረስ ብዙ ትግል አለ›› ፎቶ አንሺ፣ አይዳ ሙሉነህ

ፎቶ አንሺዋ አይዳ ሙሉነህ ኢትዮጵያ ተወልዳ በልጅነቷ ከቤተሰቦቻ ጋር ወደ የመን አቀናች፡፡ ከዛ በኋላ ካናዳ አድጋ አሜሪካ ሀዋርድ ዩኒቨርሲቲ በኮሙዩንኬሽን ትምህርት ክፍል ፊልም አጥንታለች፡፡ ከተመረቀች በኋላ በዋሽንግተን ፖስት የፎቶ ጋዜጠኛ ሆና ሠርታለች፡፡ ከኢትዮጵያ ከወጣች ከ28 ዓመታት በኋላ ተመልሳ በዋነኛነት በፎቶግራፍ ዘርፍ የሚንቀሳቀስ ደስታ ፎር አፍሪካ (ዲኤፍኤ) የሚል ድርጅት አቋቁማለች፡፡ አይዳ እ.ኤ.አ በ2007 የዩሮፓን ዩኒየን ፕራይዝ ኢን ዘ ሪኮንተርስ አፍሪካንስ ዲ ላ ፎቶግራፍና እ.ኤ.አ. በ2010 የሲአርኤኤፍ ኢንተርናሽናል አዋርድ ኦፍ ፎቶግራፍ ተሸላሚ ናት፡፡ ሥራዎቿ በአሜሪካ፣ በእንግሊዝ፣ በጀርመን፣ በማሊ፣ በደቡብ አፍሪካና በሌሎችም በርካታ አገሮች ታይተዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ፖስት ፎርዋርድ›› የተሰኘ የፎቶ መጽሐፏ ቤልጄም ታትሟል፡፡ ሥራዎቿ አሜሪካ፣ ዋሽንግተን ዲሲ ሙዚየም ኦፍ አፍሪካን አርት በቋሚነት ይታያሉ፡፡ በቅርቡ በደቡብ አፍሪካ፣  ጆሀንስበርግ አርት ፌር ሥራዎቿን ያሳየች ሲሆን፣ እሷ የምታዘጋጀው አዲስ ፎቶ ፌስት ከታኅሳስ 6 እስከ 11 ቀን 2009 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ይካሄዳል፡፡ ለአራተኛ ጊዜ የሚካሄደው ፌስቲቫሉ ከፎቶ ዓውደ ርዕይ በተጨማሪ ውይይቶችና የአፍሪካ ፎቶ አንሺዎች ውድድርም ይስተናገድበታል፡፡ በዓውደ ርዕዩ ከአፍሪካ፣ እስያ፣ መካከለኛው ምሥራቅ፣ አውሮፓ እንዲሁም ሰሜንና ደቡብ አሜሪካ የተውጣጡ ፎቶ አንሺዎች ይሳተፋሉ፡፡ በፊስቲቫሉ፣ በኢትዮጵያ የፎቶ ዘርፍ እንቅስቃሴ እንዲሁም በፎቶ ሥራዎቿ ዙሪያ ምሕረተሥላሴ መኰንን አይዳ ሙሉነህን አነጋግራታለች፡፡   
ሪፖርተር፡- የዘንድሮው አዲስ ፎቶ ፌስት ካለፉት ሦስት ዓመታት በተለየ ምን አዲስ ነገር ይዞ መጥቷል?
አይዳ፡- ለፎቶ አንሺዎች ኦፕን ኮል (ክፍት ጥሪ) ስናደርግ ዘንድሮ የመጀመርያችን ነው፡፡ በጥሪው ከዚህ በፊት የማውቃቸው ብዙ ባለሙያዎች አጋጥመውናል፡፡ በኢንዱስትሪው ከምናያቸው በተጨማሪ ከዚህ በፊት ብዙ ቦታ ያልተሳተፉ ፎቶ አንሺዎች ሲመጡ፣ የኛ ፌስቲቫል እንደ መነሻ ዕድል ይጠቅማቸዋል፡፡ ለኔ ካለመታወቃቸው ይልቅ ሥራቸው ያመዝንብኛል፡፡ ባለፈው ከ36 አገሮች የ90 ባለሙያዎችን ሥራዎች አሳይተን ነበር፡፡ ከ40 አገሮች አሁን 139 ባለሙያዎች ተውጣጥተዋል፡፡ ባለሙያዎቹ ስለኛ ፌስቲቫል አውቀው ሥራዎቻቸውን ማሳየት መፈለጋቸውን አበረታታለሁ፡፡ ከዛ ውጪ ካነን ሲረዳን ለመጀመርያ ጊዜ ነው፡፡ ሁላችንም የምንሠራው በካነን ስለሆነ ከኢንዱስትሪው ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ካነን አፍሪካ ውስጥ መሥራት ስለሚፈልግ እንደኛ ዓይነት እንቅስቃሴዎችን ይደግፋል፡፡ በዚህ ደግሞ ዘርፉም እያደገ ይሄዳል፡፡ ትልልቅ ተቋሞች ሲመጡ የገበያ ትስስር መፍጠርም ይቻላል፡፡ ዘንድሮ ከዓለም አቀፍ ሚዲያ ከፍተኛ ድጋፍ አለን፡፡ በዚህ ዓመት ቮግ ኢታልያ የኛ አጋር ተቋም ሲሆን፣ የፋሽን መጽሔቱ ግላመር ሜጋዚን የኛን የፎቶ ፌስቲቫል በተመለከተ ለመጻፍ መፈለጉ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ስለ አፍሪካ ምንም መረጃ የሌላቸው አካሎች ፌስቲቫሉን እንደ መነሻ እየተጠቀሙበት ነው፡፡ አፍሪካ ውስጥ ምን እየተከናወነ እንደሆነ የማወቅ ጉጉት እንዲያድርባቸውም ያደርጋል፡፡ ውጪ የሚሰራጨው መጥፎ ዜና ቢሆንም እኛ ማኅበረሰቡ ወደ ፊት እየሄደ መሆኑን ማሳየት እንፈልጋለን፡፡ ችግሮች ቢኖሩብንም መልካም ነገርም አለ፡፡
ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ውስጥ የፎቶውን ዘርፍ ይፈታተናሉ የምትያቸው ችግሮች ምንድን ናቸው?
አይዳ፡- በአገሪቱ በዲግሪ ፕሮግራም የፎቶግራፍ ትምህርት መኖር አለበት፡፡ የኛም ዕቅድ ትምህርት ቤት መገንባት ነው፡፡ ሁሉም ነገር በእጃችን ቢሆንም ትምህርት ከሌለ ትርጉም የለውም፡፡ መደበኛ ትምህርት የሚሰጥ ተቋም ያስፈልጋል፡፡ በየከተማው ፎቶ አንሺ አለ፡፡ በደንብ ተምረው ሳይሆን ለሙያው ፍቅር ወይም ለንግድ የገቡ ናቸው፡፡ ሌላው ፎቶ አንሺዎች ሲያነሱ ጥያቄ ይነሳባቸዋል፡፡ በርግጥ በአሁኑ ወቅት ፎቶ ማንሳት ይበልጥ ባይታሰብም፣ ከዚህ በፊትም ብዙ ውጣ ውረዶች አሳልፈናል፡፡ ከአምስት ዓመታት በፊት ለቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እኛ አገራችንን ለማስተዋወቅ እየሠራን ለምን መብታችን ይገደባል? የሚል ጥያቄ አቅርቤ ነበር፡፡ ከፍተኛ ቀረጥ ሌላው ችግር ነው፡፡ ዕቃ ከውጭ ለማስገባት ሁለት መቶ ፐርሰንት መክፈል ትርጉም አይሰጥም፡፡ ባለሙያዎች እየለፋን ዕቃዎቹ እንደ ቅንጦት ይቆጠራሉ፡፡ እነዚህን ችግሮች መፍታትና በተጨማሪም ኅብረተሰቡን ስለፎቶግራፍ ምንነት ማስተማር አለብን፡፡ በጣም ብዙ የሠርግ ፎቶ አንሺዎች አሉ፡፡ በዚህ ሁለት ዓመት ግን በቅርቡ ፎቶ ማንሳት የጀመሩ ወጣቶች ሳይቀሩ ጥሩ የሠርግ ፎቶ ሲያነሱ እያየን ነው፡፡ እኔ ሥራ የምንቅ ሰው አይደለሁም፡፡ የሠርግ ወይም የስቱዲዮ ፎቶን ለመናቅ ሳይሆን፣ ፈጠራ የታከለባቸው ፎቶዎች እየታዩ መምጣታቸውን ለመግለጽ ነው፡፡ ጥሩ ፎቶዎች መምጣታቸው የተጠቃሚዎች ዕይታ እየተለወጠ መምጣቱን የሚያሳይ ነው፡፡ ይኼንን ከፈጠራ ሥራ፣ ከታሪክ ስነዳ (ዶክመንቴሽን) እና የንግድ (ኮሜርሻል) ፎቶ ዘርፎች አንፃር መመልከት አለብን፡፡ ሐኒከን ኢትዮጵያ ከገባ በኋላ የቢራ መለያ ማስታወቂያ ገጽታ ተቀይሯል፡፡ ለዚህ መነሻው ፎቶ ነው፡፡ በግላዊ ሕይወትም ይሁን በቢዝነስ ያለው ክንውን ከፎቶ ጋር ግንኙነት አለው፡፡ በስማርትፎን የምናነሳው ፎቶም ዞሮ ዞሮ ፎቶ ነው፡፡ የሰው ግንዛቤ ቢሻሻል፣ ውድድር ይመጣና የተሻሉ ሥራዎች ይወጣሉ፡፡ ወጣት ፎቶ አንሺዎች ወደኛ ፌስቲቫል ሲመጡ የሚያዩዋቸው ፎቶዎች ይገርሟቸዋል፡፡ ከፌስቲቫሉ በኋላ ወርክሾፖች ሲሳተፉ ፎቶ ማንሳት ማለት ለካ እንዲህ ነው የሚል ሐሳብ ይሰጣቸዋል፡፡ ስለዚህ የምንሠራው ሥራ አዲስ የሚመጣውን ትውልድ የሚደግፍ ነው፡፡ ሥራቸውን በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዴት ማሳየት እንዳለባቸው ስታንዳርዱን ለማሳየትም ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የንግድ (ኮሜርሻል ፎቶግራፍ) አንድ ዘርፍ ቢሆንም ብዙ ባለሙያዎች ከዚህ ውጪ ፈጠራ የታከለባቸው ሥራዎች ባለማሳየታቸው ይተቻሉ፡፡ በዚህ ረገድ ያንቺ እንቅስቃሴ ያለውን ሚና እንዴት ትመለከቺዋለሽ?
አይዳ፡- ፌስቲቫሉ ሲጀመር ሥራቸውን ካሳዩ አምስት ኢትዮጵያውያን ፎቶ አንሺዎች ዛሬ ወደ 30 መድረሳችን ፈጠራ እያደገ እንደሆነ ያሳያል፡፡ ከዛ ውጪ በግሌ እየሠራሁ ለዓለም የማሳያቸው ሥራዎች አወንታዊ ተፅዕኖ አላቸው፡፡ እዚህ ብሠራና ብኖርም ሁሉንም ነገር የማየው ከዓለም አንፃር ነው፡፡ ከኛ በኋላ የመጡ ፎቶ አንሺዎች እንዴት በሙያው እንዳደጉ አይተናል፡፡ ብዙዎቹ ሲጀምሩ አሪፍ ፎቶ አንሺ እንደሆኑ አምነው ነው፡፡ እኔ ራሱ ብዙ ነገር ሠርቼም ገና ነኝ ነው የምለው፡፡ በፈጠራ ረገድ ወጣቶች በፌስቲቫል ሲሳተፉና ከባለሙያዎች ጋር ሲገናኙ የበለጠ መሥራት እንዳለባቸው ይገነዘባሉ፡፡ በፌስቲቫል ከተሳተፉ በኋላ ሥራቸው ቀስ በቀስ ሲለወጥ ይታያል፡፡ ለምሳሌ ያፌት ዳንኤል የሚባል ፎቶ አንሺ አለ፡፡ ፌስቲቫሉን ስንጀምር የሚሠራውንና የአሁኑን ስናነፃፅር የሚገርም ለውጥ ነው፡፡ በተመሳሳይ አሮን ስምዖን የሚባለው ባለፈው ፌስቲቫል ሥራዎቹን አላሳየም ነበር፡፡ ከኮንሠርት ፎቶ ማንሳት ወደ ፖርትሬት (ምስለ አካል) እና ታሪክ ነገራ ሄዷል፡፡ አሁን የአርበኞችን ፎቶዎች እየተከታተለ ነው፡፡ ምክንያቱም የፎቶ ሥራ መሰጠት ያስፈልገዋል፡፡ አንድ አፍታ የሚሰራ ነገር አይደለም፡፡ ፎቶ አንድ ቦታ የሚቀመጥ ስላልሆነ በየጊዜው ማደግና ሥራን መለወጥ ያስፈልጋል፡፡ በሚቀጥለው ዓመት ሁለት ውድድሮች ላይ ከሚዳኙ አንዷ ነኝ፡፡ አንዱ የሶኒ ወርልድ ፎቶ አዋርድ ሲሆን፣ በዓለም ትልቁ የፎቶ ውድድር ነው፡፡ የመጀመርያ ጥያቄዬ ከአፍሪካ ምን ያህል ፎቶ አንሺ አሳትፋችኋል? የሚል ነበር፡፡ ባንቺ በኩል ከአፍሪካ ፎቶ አንሺዎችን ለማሳተፍ ነው የፈለግንሽ የሚል ምላሽ ሰጥተውኛል፡፡ ሁለተኛው ወርልድ ፕረስ ፎቶ ውድድር፣ በጣም የተከበረ የጋዜጠኞች ውድድር ነው፡፡ ይኼንን ሁሉ ዓመት ሳስተምር፣ ፎቶ አንሺዎች በውድድሩ እንዲሳተፉ ተናግሬያለሁ፡፡ ቢያሸንፉ ባያሸንፉም ተቋሙ የሚያሳትመው መጽሐፍ ጀርባ የተሳታፊዎች ዝርዝር በየአገራቸው ይጻፋል፡፡ መጽሐፉ በዓለም አቀፍ ደረጃ የማይገባበት ቦታ ስለሌለ፣ አንድ ሰው ለሥራ ከኢትዮጵያ ፎቶ አንሺ ሲፈልግ እነሱን ያገኛል፡፡ አሁን ሁሉም ለብር ብቻ ይሯሯጣል፡፡ ለሆድ መሥራት ያለ ቢሆንም ለልብ መሥራትም ያስፈልጋል፡፡ በዓለም ታዋቂ የሚያደርገው ለልብ የሚሠራ ሥራ ነው፡፡ ለብር ብቻ ከተሠራ የዛሬ አርባና ሀምሳ ዓመታት ሥራውን የሚያስታውስ አይኖርም፡፡ በፎቶ አንሺዎች ዓለም የግል ፕሮጀክት ትልቅ ነገር ነው፡፡ እኔ የግሌን ስብስብ ሳዘጋጅ ይኼን ያህል እሸጣለሁ ወይም ተቀባይ እንዴት ያየዋል? ብዬ ሳይሆን የሚያስደስተኝን እሠራለሁ፡፡ ተቀባይነት ካገኘና ከተሸጠ ደስ ቢልም መነሻዬ ገንዘቡና መታወቁ አይደለም፡፡ መነሻዬ ማለት የምፈልገውን ከሕዝቡ ጋር መካፈሌ ነው፡፡ እዚህ አገር የሚጎለው ደግሞ ይኼ ነው፡፡ ብዙ ወጣት ፎቶ አንሺ ይኼ ዓመት ሆይ ሆይ ከሆነ ሁሌም የሚቀጥል ይመስለዋል፡፡ የሥነ ጥበብ ገበያ ፈታኝ ስለሆነ አካሄዱ እንደዚህ አይደለም፡፡ በገበያው ፈጠራ በጣም ወሳኝ ነገር ነው፡፡ እኛ የላይቲንግ (ብርሃን አጠቃቀም) ሥልጠና ስንሰጥ ሁሉም ፎቶ አንሺ በእኩል ደረጃ ይቀመጣል፡፡ ዋናው ነገር ብርሃኑ ሳይሆን ብርሃኑን ለፈጠራ የምታውሉበት መንገድ ነው እላቸዋለሁ፡፡ በተጨማሪ ይዘቱም ወሳኝ ነው፡፡ እዚህ አገር የውድድር መንፈስ ሳይሆን ገበያን ጠቅልሎ የመያዝ (ሞኖፖሊ) አካሄድ አለ፡፡ እኔ በሥራዬ ብቻ ሳይሆን ምን ያህል ሰው አፈራሁ ብዬ እጠይቃለሁ፡፡ ብዙ የሚያበሳጭና የሚፈትን ነገር ቢኖረውም ኢትዮጵያ ተመልሼ በመሥራቴ ብዙ ተምሬአለሁ፡፡ ኒው ዮርክ ሆኜ ስለዓለም ይኼንን ያህል መማር የምችል አይመስለኝም፡፡
ሪፖርተር፡- ወደ ኢትዮጵያ ስትመጪ ዘርፉ የነበረውን ገጽታ ከአሁኑ ጋር ስታነፃፅሪው ተስፋ የሚሰጥሽ፤ እንዲሁም ተስፋ የሚያስቆርጥሽ ምንድን ነው?
አይዳ፡- ብዙ ተስፋ የሚስቆርጥ ነገር ቢኖርም ኢትዮጵያውን የአገር ፍቅር አይለቀንም፡፡ ለምንድን ነው እዚህ አገር የምለፋው? ብዬ የተበሳጨሁባቸው ነገሮች ቢኖሩም በሌላ በኩል ወጣት ፎቶ አንሺዎች ስለ ፎቶ ጥበብ ሲገነዘቡና ጥሩ ደረጃ ሲደርሱ ከማየት በላይ የሚያስደስት ነገር የለም፡፡ ሁሉም ቀሽም ቢሆን ያሳዝን ነበር፡፡ ነገር ግን ብዙ አሪፍ የሚሠሩ መኖራቸውም ተስፋ ይሰጠኛል፡፡ የሕይወት ትግል የትም ቦታ ሆኜ አይቀርም፡፡ አያቴ ሁሌ ‹‹ዓለም ዘጠኝ ናትና መቼም አትሞላም፤›› ትላለች፡፡ የትም ቦታ ውጣ ውረድ ቢሆንም የፈተናው ዓይነት እንደየቦታው ይለያያል፡፡ ሁሉ ነገር በቀላሉ ከመጣ መማር ስለማይቻል ልፋት ይጠይቃል፡፡
ሪፖርተር፡- የደስታ ፎር አፍሪካ (ዲኤፍኤ) ክንውኖች ለዘርፉ ምን አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው ብለሽ ታምኛለሽ?
አይዳ፡- በዲኤፍኤ በኩል አራት ነገሮች እንሠራለን፡፡ አንደኛው በየጊዜው የምንሠጠው ነፃ ወርክሾፕ ነው፡፡ ለምሳሌ በየወሩ ፎቶ ዋክ (የፎቶ የእግር ጉዞ) እናደርጋለን፡፡ በየከተማው እየዞሩ ፎቶ ማንሳት ሲሆን፣ አዲስ የፈጠራ ሥራዎች የት እንዳሉ የምናይበት ዕድል ይሰጠናል፡፡ በሞባይል ፎቶ ማንሳት የጀመሩ ወደ ካሜራ ሲሸጋገሩ እናያለን፡፡ ንግድ ተኮር የሆነ ፎቶ ማንሳት ስናስተምር እናስከፍላለን፡፡ ሌላው (አርካይቪንግ) ፎቶ ስነዳ ነው፡፡ ለአሜሪካ ኤምባሲ ፎቶዎች ዲጂታላይዝ አድርገንና አትመን የፎቶ አርካይቨ ዓውደ ርዕይ አዘጋጅተንላቸው ነበር፡፡ ትልቁና ጊዜያችንን የሚወስደው አዲስ ፎቶ ፌስት ነው፡፡ አገሪቱ ውስጥ የፈጠራ ችሎታ እንዳለ ተመልክቻለሁ፡፡ ነገር ግን ሰው አብሮ መሥራት ስለማይችል ችሎታው ተበታትኗል፡፡ እኛ ፕሮጀክቶች እየቀረጽን አብሮ የመሥራት ነገርን ለማዳበር እንሞክራለን፡፡ በዲኤፍኤ የሁሉ ነገር መነሻችን ፎቶ ነው፡፡ ፎቶን በተለያየ መንገድ መጠቀም ይቻላል፡፡ በኅትመት፣ በዓውደ ርዕይና በመጽሐፍ መጠቀም ይቻላል፡፡ ለምሳሌ ተምሳሌት የተሰኘው መጽሐፍ ውስጥ የተካተቱትን ሴቶች ፎቶ ያነሳሁት እኔ ነኝ፡፡
ሪፖርተር፡- ከ28 ዓመታት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለስሽባቸው ምክንቶች አንዱ ከአገር ውጪ ሆነሽ ስለ ኢትዮጵያ ከምትሠሚው በተለየ አገርሽን በራስሽ ዕይታ ለመገንዘብ እንደሆነ በአንድ አጋጣሚ ገልጸሻል፡፡ አገርሽን በካሜራሽ የመገንዘብ ሒደት ምን ይመስላል?
አይዳ- ከኢትዮጵያ የወጣሁት በአምስት ዓመቴ ነው፡፡ 1992 ዓ.ም. አካባቢ መጥቼ ነበር፡፡ ከዛ በኋላ በ1999 ዓ.ም. ተመልሼ መጣሁ፡፡ ውጭ አገር ያደግኩት ሌላ ነገር ሆኜ ሳይሆን ኢትዮጵያዊ ሆኜ ነው፡፡ የካናዳ ፓስፖርት ብይዝም እንጀራ እየበላሁና አማርኛ እየተናገርኩ ነው ያደግኩት፡፡ እዛ የሚታወቀው ኢትዮጵያና እዚ ያለው ይለያያል፡፡ የኛ  ማኅበረሰብ ባህሉ የተለያየ ውስብስብ ነው፡፡ ብዙ ነገሮች አሁንም ገና ፎቶ አልተነሱም፡፡፡ የተለመደው የቄስና መስቀል ፎቶ እንጂ የማኅበረሰቡና የአገሩ ውስብስ ማንነት አልተነሳም፡፡ የግድ ገጠር መሄድ አያስፈልገንም፡፡ በየመንደሩ እጅግ አስገራሚ ታሪክ አለ፡፡ እኔም ስለ አገሩና ሕዝቡ በየጊዜው አዲስ ነገር እማራለሁ፡፡ ኢትዮጵያ የመጣሁት ለውጥ ማምጣት አለብኝ ብዬ ነው፡፡ ጭላንጭል ብርሃን ቢታየኝም እዛ ለመድረስ ብዙ ትግል አለ፡፡ እኔ ያደግኩበት አካሄድ አንድ ሰው ጥሩ ነገር ከሠራ ጥሩ ምላሽ ያገኛል የሚል ነው፡፡ በምቀኝነት አካሄድ አላደግኩም፡፡ አገሪቷ የመጽሐፍ ቅዱስ አገር ብትሆንም ብዙ መልካም ነገር ከማኅበረሰቡ መጥፋቱ ያሳዝናል፡፡ አገሪቷን ለማሳደግ አስተሳሰባችንን ቀይረን መተባበር አለብን፡፡ አገሪቷ የተገነባችው በሚለፉ ወጣቶች ነው፡፡ ሌላ አፍሪካ አገር ይኼ አይታይም፡፡ ወጣቱ ለራሱ መሮጥ ብቻ ሳይሆን ለአገር ማሰብም መቻል አለበት፡፡ ሁሉንም መርዳት ባይቻልም፣ ከማኅበረሰቡ መውሰድ ብቻ ሳይሆን ለማኅበረሰቡ ምን አበርክቻለሁ?  ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡ አሁን ሁላችንም ለራሳችን ጥቅም ብቻ እየተሯሯጥን ተበታትነናል፡፡ የሁሉም ነገር መጨረሻ ገንዘብ ማግኘት ብቻ አይመስለኝም፡፡ በተለያየ አካባቢ ያየኋቸው ችግሮች በቀላሉ የሚፈቱ ናቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ የወጣቱ ተሳትፎ ያስፈልጋል፡፡ የወደፊቱ ትውልድ ዕጣ ፈንታ በኛ እጅ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ሥነ ጥበብ ስለ አንድ አገር ወይም አህጉር የሚወራውን የመለወጥ ኃይል አለውና ለኢትዮጵያ የተሠጠውን ገጽታ በመቀየር ረገድ ፎቶ ምን ሚና ተጫውቷል?
አይዳ፡- በዚህ ረገድ ብዙ ቢቀረንም ጀምረነዋል፡፡ ስለ አገሪቱ የሚነገረው ነገር የሚለወጠው በወጣት ፎቶ አንሺዎች ነው፡፡ የማኅበረሰብ ድረ ገጽ የአገሪቱን ሌላ ገጽታ በማሳየቱ ጥሩ ነው፡፡ ምክንያቱም በመገናኛ ብዙኃን ከሚነገረው የተለየ መረጃ ይገኝበታል፡፡ ይኼ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካ ጭምርም ነው፡፡ አሁን የጥበብ ገበያው በአፍሪካ፣ በእስያና በመካከለኛው ምሥራቅ አተኩሯል፡፡ ወደ እኛ ያተኮሩት ጥበብ መሥራት የጀመርነው አሁን ስለሆነ ሳይሆን ቴክኖሎጂ ስለኛ እንዲታወቅ ዕድል ስለፈጠረ ነው፡፡ የአፍሪካ ሥነ ጥበብ በዓለም አቀፍ ደረጃ እየጎላ ሲሄድ እየታየ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ፎቶም ትልቁን ሚና ይጫወታል፡፡
ሪፖርተር፡- በፎቶግራፍ ሰነድ ከማስቀመጥ በዘለለ አንዳች ሐሳብን የመግለጽ ወይም መልዕክት የማስተላለፍ ነገር አለ፡፡ አንቺ ፎቶግራፍን በምን መንገድ ትጠቀሚበታለሽ?
አይዳ፡- እኔ የምሠራው በሦስት መንገድ ነው፡፡ አንደኛው ለሚቀጥለው ትውልድ ሰነድ ማስቀመጥ ነው፡፡ ለምሳሌ አራት ኪሎና ቦሌ ከመፍረሱ በፊት በፎቶ ዶክመንት አድርገነዋል፡፡ ማንም ሰው ከመፍረሱ በፊት የነበረውን አያስታውስም፡፡ በሌላ በኩል ሰዎች ከተወለዱበት ጊዜ ጀምሮ የነበረውን ሕይወት በፎቶ ያስቀምጣሉ፡፡ ወደ ኋላ ተመልሰው እንዲያስታውሱ የሚያደርግ ኃይል አለው፡፡ ሌላው እንደ ፎቶ ጋዜጠኛ ስብሰባ ሳነሳ ራሱ ትምህርት እወስዳለሁ፡፡ አንድ ፎቶ አንሺ በተለያየ መንገድ መሥራት አለበት፡፡ የሠርግ ፎቶ አንሺ ሠርግ ብቻ ከሚያነሳ ብዙ ነገር መሥራት ይችላል፡፡ ልዩ ልዩ ነገር መሥራት ያለው ዋጋ የገባኝ ዋሽንግተን ፖስት ስሠራ ነው፡፡ ኢንዱስትሪው ከፎቶ አንሺ ፎቶ ማንሳት ብቻ ሳይሆን ብዙ ነገር ይጠብቃል፡፡ በዓለም የታወቀው ሥራዬ ፋይን አርት ፎቶ ግራፊ ሥነ ጥበብ የታከለበት ፎቶ ነው፡፡ ስሜቴን፣ ፍልስፍናዬንና ራሴን ለመግለጽ በፎቶ ጥበብ እጠቀማለሁ፡፡ አሁን ሥራዎቼ ጆሀንስበርግና ኒው ዮርክ ይገኛሉ፡፡ የትም ቦታ ስለኔ ሲጻፍ አዲስ ፎቶ ፌስትና ኢትዮጵያ ስለሚጠቀሱ ስለኛ የማወቅ ጉጉት ይፈጠራል፡፡ ዕይታውን ወደዚህ ለማምጣት ፎቶን እንደ መሣሪያ እጠቀማለሁ፡፡ ሌሎች ፎቶ አንሺዎችም በዚህ መንገድ እንዲሄዱ አበረታታለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- አዲስ አበባ በፈጣን ለውጥ ውስጥ ያለች ከተማ እንደመሆኗ በየጊዜው የምትገኝበትን ሁኔታ ሰንዶ በማስቀመጥ ረገድ ፎቶ አንሺዎች የሚያደርጉትን ጥረት  እንዴት ታይዋለሽ? 
አይዳ፡- ከተማዋን አርካይቭ ማድረግ ዋነኛ ዓላማችን ነው፡፡ በ2004 ዓ.ም. ፎቶ አንሺዎችን በየክፍለ ከተማ ከፋፍለን ፎቶ እንዲያነሱ አድርገን ነበር፡፡ ይኼ የኛ ኃላፊነት ነው፡፡ ፕሮጀክቱ ካለቀ በኋላ የቀጠሉበትም አሉ፡፡ ሰው ትኩረት የሚሰጠው ዛሬ ሳይሆን ከዓመታት በኋላ ነው፡፡ ሙሉጌታ አየነ ሠራተኛ ሠፈርን ብቻ ሳይሆን በአካባቢው የሚኖሩ ሰዎችንም ዶክመንት አድርጓል፡፡ ብዙ ሰው የማያስተውለው ነገር ዘወትር እሑድ በቦሌ መንገድ የሚሄደውን ሰው ነው፡፡፡ ነጋዴ፣ ሀብታም፣ ደሃ፣ የገጠር ሰውና በአጠቃላይ የማይታይ ዓይነት ሰው የለም፡፡ ይኼንን በፎቶ ማስቀመጥ ያስፈልጋል፡፡ በአንድ ወቅት የሁለት ቀን ወርክሾፕ መርካቶ ውስጥ አድርገን ነበር፡፡ ይኼን ያደረግነው ፎቶ ማለት ዝም ብሎ ገጭ ማድረግ ሳይሆን የሕዝብን አኗኗር ማሳየትም ነው የሚለውን ለማስተማር ነበር፡፡ በተጨማሪም ፎቶ ሲነሳ እንዴት ከሕዝብ ጋር መግባባት እንደሚቻል ለማሳየት ነው፡፡ ሕዝቡ ፎቶው አንሺ ፈርቶ ሲያነሳ ያውቅበታል፡፡ ከሕዝብ ጋር መግባባትና መደራደር እንጂ መጣላት አያስፈልግም፡፡ አንዳንድ ሰው ፎቶ መነሳት ላይፈልግ ይችላል፡፡ በመጀመርያው ቀን ፎቶ አንሺዎቹ መርካቶ ውስጥ ተቸግረው ነበር፡፡ ከዛ በኋላ ግን ለመዱት፡፡ በፎቶግራፍ ዓለም በፎቶ አንሺና በሰው መካከል ያለው ግንኙነት ቁልፍ ነገር ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ከፎቶ ግራፎችሽ መካከል በጥቁርና ነጭ የምታነሻቸው አሉ፡፡ በተቃራኒው በጣም ደማቅ ቀለማትንም የምትጠቀሚበት ጊዜ አለ፡፡ ይኽ ተቃርኖ ምን የምታሳይበት ነው?
አይዳ፡- ለኔ ጥቁርና ነጭ ፎቶ ታሪክ ነገራ ነው፡፡ ያሉት ቀለማት ጥቁር፣ ነጭና ግራጫ ስለሆኑ በጥቁርና ነጭ ፎቶ ምንም ነገር መሸፈን አይቻልም፡፡  በፎቶሾፕ በቀለም ቦግ ማድረግ ቢቻልም ሁሌ ትርጉም አለው ማለት አይደለም፡፡ በስቱዲዮ ሥራዬ ዋና ዋና ቀለማትን ማለትም ቢጫ፣ ሰማያዊና ቀይ እጠቀማለሁ፡፡ እያንዳንዱ ቀለማት  የሚወክሉት ነገር አለ፡፡ የማየው ነገር ውስጤ ከገባ በኋላ የሚወጣበት መንገድ ይለያያል፡፡ ቀለማቸው በጣም ከገባ ቦግ ባሉት ሥራዎች ብዙ ሰው የሚማረከው ከንቬንሽናል (መደበኛ) የሆነውን ሱሪያልስቲክ (ሱሪያል የሥነ ጥበብ ሥራዎች ተቃርኖ ያላቸው ነገሮችን በማጣጣም የቀረቡ ወይም በቅርበት ሲታዩ ተመልካቹ ከመጀመርያው ዕይታ የተለየ ትርጉም የሚያገኝባቸው ናቸው፡፡) በሆነ መንገድ ስለሚቀርቡ ነው፡፡ በቀለሞቹ ማስደንገጥ እፈልጋለሁ፡፡ ነገር ግን ከቀለሞቹ ጀርባ ብዙ ታሪክ ይገኛል፡፡ በቀለሙ ተመልካችን አስባለሁ፡፡ በደንብ ሲመለከት ጨለምተኛ የሆነ ነገር ይታያል፡፡ ቀለም መቀባቴ ትራዲሽናል አፍሪካን ቦዲ ፔይንት (ከአፍሪካ ባህላዊ የሰውነት ቀለም ቅብ) በመነሳትም ነው፡፡ ለእነዚህ ሥራዎች ያገኘሁት ምላሽ አስደሳች ነው፡፡ አፍሪካ ውስጥ ባህላዊ የሚባሉ ነገሮች በዕውን ዘመናዊ ናቸው፡፡ እኛ ግን ዘመናዊ ለመሆን ባህሉን ጥለን ዝብርቅርቅ ወዳለ ነገር እየገባን ነው፡፡ የሰውነት ቀለም ቅብ፣ አጊያጌጥና አለባበሱ ፈጠራ የተሞላ ነው፡፡ እኔ የማየው ባህላዊ እሴቶችን ከራሴ ምልከታ ጋር በማዋሃድ ወደ ቀጣዩ ትውልድ ከማሸጋገር አንፃር ነው፡፡ ሥራዬ  ከእኔ ሕይወት ተሞክሮ የተለየ አይደለም፡፡ ለምሳሌ ሰውነቷን ነጭ ቀለም ተቀብታ ቀይ ቀለም በተቀባ እጅ የተያዘችው ሴት ፎቶ ስለምቀኝነት ነው፡፡ ወደፊት ለመሄድ ጭንብል መልበስ አለብን፡፡ ትግል ውስጣችን ካለው ስሜትና ውጪ ካለውም ነገር ጋር ነው፡፡ በዚህ መሀል እኔ ያጣሁት እውነት የሚባለውን ነገር ነው፡፡ ጭንብላችንን ገልጠን እውነት የሚባለውን የምናየው መቼ ነው? የሚለውን ጥያቄ ለማንሳት ነው፡፡ ይኼንን በጥበብ እገልጸዋለሁ፡፡ በብዛት የምሠራቸው ነገሮች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋርም ይገናኛሉ፡፡ ለሥራዬ ከሚያነሳሱኝ ነገሮች መካከል ሰብዓዊነታችን የቱ ጋር ነው? የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ በዓለም ብዙ የሚረብሹ ነገሮች ስናይ ሃይማኖት የት ነው? ብለን እንጠይቃለን፡፡ ይኼ ሁሉ ቴክኖሎጂ ባለበት ዓለም ብዙ መጥፎ ነገር ሲፈጠር የኛኑ ክፋት ያሳያል፡፡ የእዚህ ዓለም ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ምንድን ነው? ብለን የምንጠይቅበት ወቅት ላይ ነን፡፡ ስለነዚህ ጉዳዮች በሥራዎቼ አማካይነት ውይይት እንዲፈጠር እፈልጋለሁ፡፡ ‹‹99 ሲሪስ›› የተባለው ሰባት ፎቶዎች ያሉት ስብስብ በዳንቴ ‹‹ዘ ዲቫይን ኮሜዲ›› ግጥም ተነሳስቼ የሠራሁት ነው፡፡ ‹‹ዘ ውልፍ ዩ ፊድ›› የተሰኘው ደግሞ የፐርኪን አባባልን የተመረኮዘ ነው፡፡ ‹‹ዘ ወርልድ ኢዝ ናይን›› የሚለው የፎቶ ስብስብ ‹‹ዓለም ዘጠኝ ናት›› ከሚለው አባባል የተወሰደ ነው፡፡ በሁሉም ሥራዎቼ ጥያቄ እጠይቃሁ፡፡ እውነታን በሚያስጠላ መንገድ ማሳየት እንችላለን፡፡ ይኼንን መንገድ ግን ሰው ለምዶታል፡፡ ለምሳሌ የሲሪያን በቦንብ መደብደብ ሰው ስለለመደው ሲመለከተው ምንም አይመስለውም፡፡ እኔ ባለኝ ሙያ ማኅበረሰቡ እንዲጠይቅ በማድረግ ለውጥ ማምጣት አለብኝ ብዬ አስባለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- ‹‹99 ሲሪስ› ና ‹‹ዘ ውልፍ ዩ ፊድ›› የተሰኙት የፎቶ ስብስቦች ቁጣ፣ ተስፋ መቁረጥ፣ ጽልመትን ያሳያሉ፡፡ በእነዚህና በሌሎችም ሥራዎችሽ መናገር የምትፈልጊውን ተመልካቾች ይገነዘቡታል ብለሽ ታምኛለሽ?
አይዳ፡- በቅርቡ በጆሀንስበርግ አርት ፌር ሥራዎቼ ሲቀርቡ ከሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች እስከ ትልልቅ ሰዎች ተገኝተው ነበር፡፡ እኔም ስለፎቶዎቹ ለማስረዳት በቦታው ነበርኩ፡፡ ሥራዎቼ ሲታዩ ውይይት የሚካሄድባቸው ነገሮች እኔ በሥራዎቼ እንዲነሱ የምፈልጋቸው ናቸው፡፡ ይህ ማለት ሰው ተረድቶታል ማለት ነው፡፡ እኔ በዚህ ምድር ያለሁት ዓለምን ለማትረፍ ሳይሆን እግዚአብሔር በሰጠኝ ዕውቀት የአቅሜን ለማበርከት ነው፡፡ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ሥራዎችሽ አነሳስተውናል፣ እኛ ማለት የፈለግነውን ብለሽልናል የሚሉ ምላሾች አግኝቼአለሁ፡፡ መልዕክት ማስተላለፍ የሚቻልበት መንገድ ሲኖር ዕውነታውን ማሳየት ያስፈልጋል፡፡ አፍሪካ እየተለወጠች ያለች አኅጉር ናት፡፡ ብዙ ሰው ወደ አኅጉሪቷ መጥቶ ለራሱ ጥቅም ብቻ ስለሚቦጫጭቅ ሥራዎች ቀጣይነት የላቸውም፡፡ እኔ የምሠራው ቀጣይነቱ እንዳይጠፋ ነው፡፡ ወደፊት እንደኔ ዓይነት ወይም ከኔ የተሻለ ሰው መጥቶ መንገዱን እንዲቀጥል እፈልጋለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- ዓለምን የሚፈታተኑ ብዙ ነገሮች ባሉበት ሁኔታ የኔ ዕውነታ የምትይው ነገር ምንድን ነው?
አይዳ፡- ለኔ ጥሩና መጥፎ ታሪኮች እኩል የሚቀርቡበት አማካይ ቦታ ዕውነታ ነው፡፡ አሁን ያለንበት ትውልድ ጥሩውን ማውጣት መቻል አለበት፡፡ ይኼ አገር ሁሌ በመጥፎ ሆኔታ እየታየ እዛ ላይ መጨመሩ ትርጉም የለውም፡፡ በቤት፣ በከተማ፣ በአገርና መጨረሻ ላይ በዓለምም ጥሩም መጥፎም አለ፡፡ ይኼንን ማስማማት መቻል አለብን፡፡
ሪፖርተር፡- ‹ሶ ሎንግ ሌተር›› (የስንብት ደብዳቤ) የሚል የፎቶ ዓውደ ርዕይ አዲስ አበባ ውስጥ አሳይተሽ ነበር፡፡ ሴትነትን በፎቶዎችሽ ስለገለጽሽበት ሁኔታ ብታብራሪልን?
አይዳ፡- ‹‹ሶ ሎንግ ኤ ሌተር›› የተሰኘውን የሴኔጋላዊቷ ሜሪማባ መጽሐፍ መነሻ ያደረገ ነው፡፡ መጽሐፉን ትምህርት ቤት ተምረንበት ነበር፡፡ መጽሐፉ ውስጥ ያለችው ገፀ ባህሪ ለጓደኛዋ ከአፍሪካ ደብዳቤ ትጽፋለች፡፡ በደብዳቤዋ ስለ ሕይወቷና ስለ ሴት ትግል ትጽፋለች፡፡ ለምሳሌ ባሏ ሌላ ሴት ጋር ሲሄድና ሌሎችም ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ብዙ ጊዜ በሥራዎቼ የማነሳው ስለ ሴት ነገር ነበር፡፡ በወንድ ላይ የማተኮር ፍላጎት የለኝም፡፡ ተምሳሌት የተሰኘው የኢትዮጵያውያት ሴቶች ታሪክ የያዘ መጽሐፍ ሲሠራ ወደ 60 ሴቶች ፎቶ ያነሳሁትም ለዚህ ነው፡፡ ‹‹ሶ ሎንግ ኤ ሌተር››ን ሁሌ አስበው ነበርና ካነሳኋቸው ፎቶዎች መካከል ሴቶችን የሚገልጹትን መርጬ ዓውደ ርዕይ ለማሳየት ወሰንኩ፡፡ ብዙ ሰው ፌምኒስት ነሽ ወይ? ብሎ ይጠይቀኛል፡፡ እኔ የማስበው እንደዛ አይደለም፡፡ እኔ ሴት ነኝ፣ እናት ነኝ፣ ሚስት ነኝ፣ ነገር ግን የትም ቦታ የምገባው ሴት ነኝ ብዬ ሳይሆን አይዳ ነኝ ብዬ ነው፡፡ የትም ቦታ ስገባ ጥቁር ሆኜ አይደለም፡፡ በዚህ መሠረት የሚማርኩኝን ነገሮች እሠራለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ተወልደሽ ልጅነትሽን የመንና ካናዳ አሳልፈሻል፡፡ በተለያዩ አገሮች እየተዘዋወርሽ ከማደግሽ ባሻገር ልጅነትሽን እንዴት ትገልጪዋለሽ?
አይዳ፡- ብዙ ሰው የአምባሳደር ልጅ መሆኔን ያያል፡፡ ነገሩ ግን እንዳዛ አይደለም፡፡ ብዙ አገር የተዘዋወርነው እናቴ ሁሌ የተሻለ የመኖሪያ ቦታ ስለምትፈልግ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ወለደችኝ፣ ካናዳ አስተማረችኝ፣ አሜሪካ አሳደገችኝ፡፡ አስተዳደጌ ለዓለም ያለኝ አተያይ የተለያየ እንዲሆንና የትም ቦታ ሄጄ ከሰው ጋር መግባባት እንድችል ረድቶኛል፡፡ ከዛ ውጪ ካሳለፍኳቸው ነገሮች አንፃር ሕይወቴ ቀላል አልነበረም፡፡ ብዙ ጊዜ ከቦታ ቦታ እንጓጓዝ ስለነበር የረዥም ጊዜ የምለው ጓደኛ የለንም፡፡ እንደዛም ሆኖ በልጅነቴ ያሳለፍኳቸው ነገሮች ጥንካሬ ሰጥተውኛል፡፡ ሁሉም ነገር የሚመች ቢሆን ኖሮ ምንም አልሠራም ነበር፡፡ የተሻለ ነገር የሚሠራው ሳይመች ሲቀር ነው፡፡ የካናዳ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ያዘጋጀኝ ለዩኒቨርሲቲ ብቻ ሳይሆን ለሕይወት ጭምርም ነው፡፡ እስከ ዛሬ የምጠቀመው ዩኒቨርሲቲ የተማርኩትን ሳይሆን እዛ ያገኘሁትን ነው፡፡ እዛ ሳድግ የማስበው የማላውቀው አገር ኢትዮጵያን ነበር ሳየው ከሌላ ሰው አገር በራስ አገር መጥቶ መከራከር ይሻላል፡፡ Read from the source

No comments:

Post a Comment