የኢትዮጵያ ሃገራዊ ንቅናቄ በሚል ስም የሚጠራ የፖለቲካ ድርጅት ትናንት፤ ዕሁድ ዋሺንግተን ዲ.ሲ. ላይ በተፈረመ ስምምነት መቋቋሙ ተገለፀ፡፡
ዋሺንግተን ዲሲ —
ድርጅቱን የመሠረቱት አርበኞች ግንቦት ሰባት፣ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር፣ የአፋር ሕዝብ ፓርቲና የሲዳማ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ መሆናቸውን አደራዳሪና አፈራራሚ ከነበሩት መካከል አንዱ የሆኑት በኢሊኖይ ቺካጎ የኢኮኖሚክስ ፕሮፌሰር ዶ/ር ጌታቸው በጋሻው ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት ማብራሪያ ገልፀዋል፡፡
የንቅናቄው ዓላማ የግዛት አንድነቷ የተጠበቀ፣ ዴሞክራሲያዊ የሕዝብ መብቶች የተከበሩባት፣ የፖለቲካ ሥልጣን ከላይ እስከታች በተዋረድ ያሉትና በምርጫ የሚጨበጥ ሥልጣን የሚኖራትን ፌደላዊት ኢትዮጵያን መመሥረት መሆኑን ዶ/ር ጌታቸው ገልፀዋል፡፡
የትግላቸው ግብ የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም፤ አዲስ ሕገመንግሥት እንዲቀረፅና ሁሉም ዜጋ እኩል የሆነባት ፌደራል ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መፍጠር መሆኑንም አደራዳሪው አስታውቀዋል፡፡
ንቅናቄው አኀዳዊ ፓርቲ እንዳልሆነ የገለፁት የምሥረታው ሂደት አመቻች ከሁሉም አባል ድርጅቶች የተውጣጣ የወኪሎች ምክር ቤት፣ የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴና የአማካሪዎች ምክር ቤት የሚኖረው አባላቱ በተናጠል የሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች እንደተጠበቁ ሆነው በአንድ አመራር ሥር የሚንቀሣቀሱበት መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
የትግላቸው ሥልት ለሰላማዊ የሕዝብ እምቢተኝነት መሥራት መሆኑን ዶ/ር ጌታቸው ገልፀው ሁሉም ድርጅቶች ግን የየራሣቸውን የትግል ሥልት መከተል እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡
የንቅናቄው መሪዎች እንዲሆኑ የተመረጡት አቶ ሌንጮ ለታ፣ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋና ዶ/ር ዲማ ኖጎ መሆናቸውንም ዶ/ር ጌታቸው አክለው አመልክተዋል፡፡
ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ፡፡ Read more here
ስለኢትዮጵያ አገራዊ ንቅናቄ መመሥረት ዶ/ር ጌታቸው በጋሻው ከቪኦኤ ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ ከሥር ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ፡፡
No comments:
Post a Comment