Sunday, October 9, 2016

የኦሮሞ ቻርተር ጉዳይ ወዴት ያደርሰናል? – ሰማሀኝ ጋሹ (ዶ/ር)

ሰማሀኝ ጋሹ (ዶ/ር)
የኦሮሞ ቻርተርና ወታደራዊ ክንፍ መቋቋምን በተመለከተ የሚመክር በአትላንታ የሚካሄድ ስብሰባ ዜና እና ሰነድ ይፋ ከተደረገ በሗላ በተለያዩ ወገኖች ዘንድ ጥርጣሬና ጥያቄ አስነስቷል። ጋዜጠኛ ሳዲቅ አህመድ አቶ ጃዋርንና ፕ/ር ህዝቄልን የኦሮሞ  ቻርተርን በተመለከተ ውይይትም አካሂዷል። በውይይቱ ወቅት የመገንጠል ጥያቄዉን በተመለከተ ጥሩ ማብራርያ የተሰጠ ቢሆንም አሁንም በርካታ መልስ የሚሹ ጉዳዮች አሉ። በተለይ አትላንታ ይካሄዳል ተብሎ የታሰበዉን ስብሰባ በተመለከተ የወጣዉ መግለጫ በብዙዎች ዘንድ ያልተጠበቀ ነገር ነዉ። በጎንደር በተካሄዳዉ የተቃዉሞ ሰልፍ ወቅት ህዝቡ ‘ የኦሮሞ ደም የኛ ደም ነዉ’  ፥ ‘ በቀለ ገርባ መሪያችን ነዉ’ በማለት ለኦሮሞ ህዝብ የተቃዉሞ እንቅስቃሴ ያለዉን አጋርነት ከገለፀ በሗላ በህዝቦች መካከል የነበረዉንና በህወሓት ለዘመናት የሚዘወረዉን የከፈፍልህ ግዛ (divide and conquer)  ፖለቲካ በማዳከም ከፍተኛ የትግል አንድነት ያመጣ መሆኑ ይታወቃል። ህዝቡ ይህንን የተፈጠረዉን አንድነት የሚያጠናክር የፖለቲካ ሀይሎች የጋራ መድርክ ሲጠብቅ የተናጥል ስብሰባ መጠራቱ በብዙዎች ዘንድ ጥርጣሬ መጫሩ የሚጠበቅ ነዉ። ከዚህ አኳያ የተፈጠረዉን የህዝብ አንድነት ሊያጠናክር የሚችል ስራ ላይ ማተኮር ሲገባ የተናጠል የስብሰባ ጥሪ መጠራቱ  በጋራ ትግሉ ላይ የራሱን ተፅእኖ ማሳደሩ የማይቀር ነዉ።
ከዚህ የከፋዉ ደግሞ የቀረበዉ ሰነድ ስለ ህዝቡ የጋራ ትግልና የደረሰበትን ደረጃ  ጨርሶ አያነሳም።  ሰነዱ ወደፊት የኦሮሞ ህዝብ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ስርአት ዉስጥ የሚኖረዉን ሚና በተመለከተም ምንም አይነት ፍንጭ ያልሰጠ ሲሆን   የኦሮሞን ህዝብ በደሴትነት ተነጥሎ የተቀመጠ ያስመስለዋል። እንደዉም ሰነዱ የኦሮሞ ህዝብ ከኢትዮጵያ ጋር ያለዉን ግንኙነት የቅኝ ግዛት አድርጎ ያቀርበዋል። የቅኝ ግዛት ትንታኔዉን (colonial thesis) በርካታ የኦሮሞ ምሁራንና ፖለቲከኞች እንደማይደግፉት እየታወቀ ሁሉንም የኦሮሞ መሪዎች ላማሰባሰብ ያለመ ሰነድ ለምን ያአንድ ወገን አቋም ብቻ ለማንፀባርቅ እንደፈለገ ግልፅ አይደለም። የኦሮሞ ህዝብ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ያለዉን ግንኙነት የቅኝ ግዛት ጥያቅ እንዳልሆነ የሚያምኑትን የኦሮሞ ፖለትከኞችና ምሁራን የሚያገል ያሰመስለዋል። የኦሮሞን ህዝብ ቅኝ እንደተገዛ አድርጎ ማቅረቡ የኦሮሞ ህዝብ ከሌላዉ ህዝብ ጋር ያለዉን የባህልና የታሪክ ትስስርና የኦሮሞ ህዝብ ለኢትዮጵያ አንድነትና ህልዉና ያበረከተዉን አስተዋፅኦ የሚያሳንስ ነዉ። ከዚህም በተጨማሪ ይህን አይነቱ ትንታኔ አንዱን ማህበረሰብ ጨቋኝ ሌላዉን ተጨቋኝ በማድረግ የሚቀርበዉን የታሪክ ትንታኔ ህያዉ ሆኖ እንዲቆይ የሚፈልግ ያስመስለዋል። ይህም  እስካሁን የሄድንበትን የጋራ አለመተማመን (mutual suspicion) በማስቀጠል ልንፈጥረዉ ለምናስበዉ ዴሞክራሲያዊ ስርአት እንቅፋት ይሆናል።
በተለይ በኢትዮጵያን አንድነትና በግለሰብ መብት ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ስርአት እንዲቋቋም የሚፈልጉ ዜጎችን የቀድሞዉ ስርአት ናፋቅዎችና ምኒልካዉያን እየተባለ መስደብ የተለመደ ነዉ። ያሁኑን ተዉልድ የፖለቲካ አስተሳሰብ መተቸት ካስፈለገ በራሱ በትዉልዱ አስተሳሰብ ላይ ተመስርቶ መተቸት ሲገባ ከቀደሙት ስርአቶች ጋር በማያያዝ አንገት ለማስደፋት የሚደረገዉ እንቅስቃሴ ያደባባይ ሚስጥር ነዉ። የዚህ ፅሁፍ አቅራቢ ከወራት በፊት ያደረገዉን የሬድዮ ዉይይት አስመልክቶ የቀድሞዉ ስርአት ናፋቂ የሚል ስድብና ዛቻ የኦሮሞ አክቲቪስቶች ነን ከሚሉ ወገኖች አስተናግዷል። ለዚህም ነዉ የአማራ ወጣቶች ሁሉም የብሄር ድርጅቶች አማራን በጠላትነት የሚፈርጁ በመሆኑ ተደራጅተን እራሳችንን እንከላከል እያሉ ያሉት። ምንም እንኳን ያለፈዉን ታሪካችንን በተመለከተ ብሄራዊ መግባባት ላይ መድረስ አስቸጋሪ ሊሆን ቢችልም እንዲህ አይነት የታሪክ ትንታኔዎችን ለፖለቲካ ፍጆታ ባለመጠቀም የተሻለ የፖለቲካ ድባብ ለመፍጠር ጥረት እንዳልተደረገ ግን ከቀረበዉ ሰነድ መረዳት ይቻላል።
ከዚህም በጠጨማሪ የቀረበዉ ሰነድ ባለፉት አስርተ አመታት የብሄረሰቦችን እኩልነት ለማምጣት የተሄደበትን መንገድ፥ ዉጤቱንና ችግሮቹን ሳያነሳ የኦሮሞ ህዝብ ከዛሬ አርባ አመት በፊት በነበረበት ሁኔታ እንዳለ አድርጎ ያቀርበዋል። ከሁሉም ብሄረሰቦች የተወጣጡ ወጣቶች በተማሪዎች እንቅስቅሴ ወቅት ያነሱት የመሬት ላራሹና የራስን እድል በራስ የመወሰን ጥያቄ በደቡብ ኢትዮጵያ የነበረዉን የጭሰኝነት ስርአት ያስወገደ ሲሆን ይህም ለኦሮሞ ህዝብ ታላቅ ለዉጥ አምጥቷል። ደርግም ሆነ ወያኔ ስታሊናዊ በሆነ መንገድ ችግሮቹን ለመፍታት የሄዱበት መንገድ ዉጤቱ አመርቂ ባይሆንም ሙከራዎች ግን ተደርገዋል። ይህ ሁሉ የፖለቲካ ለዉጦች በተካሄዱበት ሀገር አሁንም ቅኝ እንደተገዛን ነን የሚል እድምታ ያለዉ አቀራረብ በጣም ጨለምተኛና  ካላፈዉ ስህተቶች ተምሮ የቀረዉን የእኩልነት ጥያቅ ለማሳካት በሚያስችል መልኩ አለመቀረፁ በኢትዮጵያ ያለዉን አስቸጋሪ የፖለቲካ ሁኔታ ለመፍታት ያለዉን ቁርጠኝነት ዉሱን ያስመስለዋል።
የኦሮሞ መሪዎች ስብሰባ ያስፈለገበትን ምክንያት አቶ ጃዋር ሲያስረዳ ወደፊት ለሚደረገዉ የሽግግር ወቅት እያንዳንዱ ማህበረሰብ የራሱን ቻርተር አዘጋጅቶ መምጣት ስላለበት የኦሮሞን ቻርተር  ለማዘጋጀት በማስፈለጉ ነዉ ይላል። ለዚህም የደቡብ አፍሪካዉን ብሄራዊ ኮንግረስና የህንዱ ጃዋራላል ኔህሩ በትግል ወቅት እንዲህ አይነት ቻርተር አዘጋጀተዉ ነበር ሲል ያስረዳል አቶ ጃዋር። እያናንዳንዱ ማህብረስብ የራሱን ቻርተር አዘጋጅቶ ይምጣ ከተባለ  ሁሉም ብሄረሰቦች አንዳንድ ቻርተር በማዘጋጀት ሲመጡ ቢያንስ ከ 80 ያላነሱ ቻርተሮች ተዝጋጅተዉ ሊቀርቡ ነዉ ማለት ነዉ( ያዉም እያንዳንዱ ማህበረሰብ በአንድ ድርጅት ይወከላል ብለን ካሰብን ነዉ።) እንዲህ ያለ ሁኔታን እንዲኖር መፈለግ አላማዉ ዴሞክራሲያዊ ስርአት ወይስ የባቢሎንን ግንብ ለመገንባት ነዉ? ሁሉም ብሄር የራሱን መብት እንዲከበር በሚል በሚያደርገዉ ፍላጎት ሁሉንም የሚያረካ መፍትሄ ማግኘት የሚክብድ ከመሆኑም በተጨማሪ የፈለገዉን ያላገኘዉ ወገን ‘የራሴን እድል በራሴ’ እወስናለሁ ወደሚል ሌላ ዙር ግጭት ይገባል። በተለይ ወታደራዊ ክንፍ ያለዉ የብሄር ድርጅት የሚበረታታ ከሆነ በጉልበት የፈለገዉን ለማድረግ ማንገራገሩ የማይቀር ነዉ። ወያኔም በ1983 ዓም ባደረገዉ የሽግግር መንግስት ምስረታ ወቅት በብሄር የተደራጁትን ብቻ ተቀብሎ ህብረ ብሄር የሆኑትን ግን አልቀበልም ነበር ያለዉ። ለዚህም የተማመነዉ የነበረዉን ጉልበት ነዉ። ኦነግንም ከሽግግሩ መንግስት እንዲወጣ ያደረገዉ ይሄዉ የወያኔ እብሪተኝነት ነዉ። አሁንም በብሄር ተደራጅታችሁ የራሳችሁን ቻርተር አዘጋጅታችሁ ኑ ማለት ተመሳሳይ አካሄድ ያለዉ ነዉ። በርካታ ማህበረሰቦችም በተለያየ ምክንያት ተደራጅተዉ  ቻርተር አዘጋጅተዉ ላይቀርቡ ይችላሉ። በዚህ ጊዜ የነዚህ ማህበረሰቦች እድል ቻርተር አዘጋጅተዉ በመጡት ሊወሰን ነዉ ማለት ነዉ? ይህስ አካሄድ ወያኔ በ1983 ካደረገዉ በምን ይለያል? ወታደራዊ ክንፍ ያላቸዉ የፖለቲካ ሃይሎች እኛ ባልነዉ ካለተስማማችሁ ዞር በሉ ቢሉ ዋስትናዉ ምንድን ነዉ? አልሸሽም ዞር አሉ እንደሚባለዉ ተመልሶ ወደ ግጭት አያስገባንም ወይ?
አቶ ጃዋር ያቀረባቸዉ የደቡብ አፍሪካ፤ ህንድና ቱኒዝያ ምሳሌዎች አሁን ከተጠራዉ የኦሮሞ የነፃነት (freedom) ቻርተር ጉዳይ በጣም የተለዩ ናቸዉ። በነዚህ ሃገሮች የቀረቡት የነፃነት (freedom) ቻርተሮች ሆነ ድርድሮች ሃገራዊና የሁሉንም ማህበረሰብ ፍላጎት የሚያንፅባርቁ እንጂ የአንድ ብሄርን ብቻ የሚመለከቱ አልነበሩም። እንዲሁም በህንድ የተካሄደዉ የፀረ ቅኝ ግዛት ትግልና በደቡብ አፍሪካ የተካሄደዉ የፀረ አፓርታይድ ትግል አሁን ኢትዮጵያ ዉስጥ ካለዉ የፖለቲካ ሁኔታ ጋር ያላቸው ዝምድናና እና ልዩነት በግልፅ አልቀረበም ። የምናቀርባቸዉ ምሳሌዎች ተገቢ ትርጉማቸዉን የያዙ ቢሆኑ የምናቀርበዉን ሃሳብ ተአማኒነት ያጠናክረዋል። አቶ ጃዋር ስለ ቱኒዝያ የተናገረዉም እኛ እየሄድንበት ካለው ጋር የሚገናኝ አይደለም። ከሌሎች አብዮት ከተካሄደባቸዉ የአረብ ሃገራት በተለየ የተሻለ የፖለቲካ ሽግግር በቱንዝያ የተፈጠረዉ እንደ ሊቢያና ሶርያ በሃይማኖትና በጎሳ ለመከፋፈል ባለመፍቀዳቸዉ ነዉ። ወታደራዊ ክንፍ ያላቸዉ የብሄር ድርጅቶችን የምናበረታታ ከሆነ ግን ለጊዜዉ በአንድ ጠላት ላይ ሲያተኩሩ ልዩነት የሌላቸዉ የሚመስሉ የፖለቲካ ህይሎች ያ ጠላት ከስፈራዉ ሲነሳ  እርስ በርሳቸዉ መበላላታቸዉ የማይቀር ነዉ።  ሊብያ ዉስጥ በተካሄደዉ አብዮት ወቅት ሁሉም ጎሳዎች ጋዳፊን ለመጣል ሰምና ወርቅ ሆነዉ ከሰሩ በሗላ አሁን ሁሉም በየፊናዉ  ወታደራዊ ቀጠና አቋቁሞ እየተጋጨ ሲሆን ማዕከላዊ መንግስት በስምምነት ለመመስረት አልቻሉም ።
በእዉነት የኢትዮጵያን የፖለቲካ ችግሮች ለመፍታት ቅንነቱና ቁርጠኝነቱ ካለ እንደ ኑክልየር ሳይንስ ዉስብስብ ስላልሆነ 80 ቻርተር ማዘጋጀት አያስፈልገዉም። የኢትዮጵያ የፖለቲካ መሰረታዊ ችግሮች እንዴት ብሄራዊ አንድነትንና የብሄር  መብትን፥  የግለሰብና የቡድን መብትን አጣጥመን እንቀጥል፥  እንዴት ብሄራዊ መግባባትን እንፍጠር፥ ዴሞክራሴያዊ ባህልና ተቋማት እንዴት እንገንባና ማህበራዊና ኤኮኖምያዊ ፍትህ እንዴት እናረጋግጥ የሚሉት ናቸዉ። እነዚህን የፖለቲካ ጥያቄዎች ለመመለስ ዋናዉ መነሻ የተናጥል አካሄድን በተቻለ መጠን በማስቀረት ሁሉም የፖለቲካ ሃይሎች በጋራ የሚመክሩበትን ሁኔታ ማመቻቸት ነዉ። ነገር ግን አሁንም የሽግግር ሂደቱን በበላይነት ለመቆጣጠር የሚካሄደዉ ፉክክር ስር የሰደደዉን የፖለቲካ ሃይሎች አለመተማመን እንዲቀጥል የሚያደርገዉ ከመሆኑም በተጨማሪ የግጭትንና የእኔ አውቅልሃለሁን የቆየ የፖለቲካ ባህል ለመለወጥ የሚኖረዉን እድል ያደበዝዘዋል። Read more here 

No comments:

Post a Comment