አቶ ሙሉጌታ አረጋዊ፣ የዓለም አቀፍ ሕግ ባለሙያና ጠበቃ
አቶ ሙሉጌታ አረጋዊ መቀመጫቸውን በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ያደረጉ የዓለም አቀፍ ሕግ ባለሙያና ጠበቃ ናቸው፡፡ አቶ ሙሉጌታ በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪ (ኤልኤልቢ) ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሕግ ትምህርት ቤት ያጠናቀቁ ሲሆን፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን (ኤልኤልኤም) ከዋሽንግተን የሕግ ኮሌጅ በዓለም አቀፍ ሕግ አግኝተዋል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ቤት የሕገ መንግሥት ጥናትን ጨምሮ የተለያዩ ትምህርቶችን አስተምረዋል፡፡ በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ሐሳባቸውን በነፃነት በማካፈልም ይታወቃሉ፡፡ ሰለሞን ጎሹ በወቅታዊ ጉዳዮችና በሕገ መንግሥቱ ላይ አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ረዘም ላለ ጊዜ የቆዩ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች አሉ፡፡ መንግሥት እነዚህን ጥያቄዎች የተረዳበትንና ምላሽ የሰጠበትን መንገድ፣ እንዲሁም ችግሮቹን በዘለቄታው ለመፍታት ያስችላሉ በማለት የያዛቸውን ዕቅዶች እንዴት ይገመግሙታል? 
አቶ ሙሉጌታ፡- አሁን ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት በሥልጣን ላይ ለ25 ዓመታት ቆይቷል፡፡ በኢኮኖሚው ረገድ በእነዚህ ዓመታት ጥሩ ሥራ የሠራ ይመስለኛል፡፡ ብዙ ሰዎችም የሚያምኑ ይመስለኛል፡፡ በፍትሕና በሕግ ጥያቄ ላይ ግን ችግር እንዳለበት መንግሥት ራሱ ያምናል፡፡ መልካም አስተዳደር አልሰጠሁም ብሏል፡፡ ሙስናን መቆጣጠር እንዳልቻለ፣ ይልቁኑም ከጊዜ ወደጊዜ እየተባባሰ እንደሄደ ተገልጿል፡፡ ከሙስና ጋር ያለው ልዩነት ለእኔ ግልጽ ባይሆንም፣ ኪራይ ሰብሳቢነት የሥርዓቱ አደጋ የሆነበት ጊዜ እንደሆነ መንግሥት ራሱ ያምናል፡፡ ሌላው ቀርቶ የመንግሥት ሥልጣንን ለግል ጥቅማቸው የሚያውሉ ባለሥልጣናት እንዳሉም መንግሥት አምኗል፡፡ ስለዚህ አንድ መንግሥት መልካም አስተዳደር መስጠት አልቻልኩም ካለ ምንድነው መደረግ ያለበት? ለእኔ እንደሚገባኝ መንግሥት ተጨማሪ ጊዜ ይሰጠኝ እያለ ነው፡፡ እንደገና እታደሳለሁ እያለ ነው፡፡ ከ15 ዓመታት በፊትም ገዢው ፓርቲ እታደሳለሁ ብሎ ነበር፡፡ ሁለቱ ግን የተለያዩ ናቸው፡፡ የበፊተኛው መነሻ በአንድ ድርጅት ውስጥ የተፈጠረ መከፋፈል ነው፡፡ ሕወሓት በመከፋፈሉ የመጣው ችግር የወለደው ነበር፡፡ እውነት ነው ችግሩ ከሕወሓት አልፎ ሌሎቹንም ድርጅቶች ነካክቶ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ግፋ ቢል ችግሩ የኢሕአዴግ ነው የነበረው፡፡ ራሱ በስብሻለሁ አለ፡፡ ሳይገደድ እታደሳለሁ አለ፡፡ በዚህ መሠረት የተሃድሶ ፕሮግራም አካሂጃለሁ አለ፡፡ አሁን ግን መንግሥት ፈልጎ አይደለም፡፡ አሁን መንግሥት ላይ ጫና እየተደረገበት ነው፡፡ ሕዝብ ለወራት ተቃውሞ እያሰማ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ከዚህ ቀደም ያላየነው ዓይነት ተቃውሞ ነው እየታየ ያለው፡፡ ስለዚህ ሁለቱ የማይገናኙ ተሃድሶዎች ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ውስጣዊ የፓርቲ  ችግር ነው፡፡ የአሁኑ ግን በአንድ በኩል መንግሥት በሌላ በኩል ሕዝቡን ያካተተ ችግር ነው፡፡ መንግሥት ችግሮች አሉብኝ ካለ ችግሮችን እንዴት እንፍታቸው ለሚለው መንግሥት፣ ሕዝቡና ተቃዋሚ ፓርቲዎች የተለያዩ የመፍትሔ ሐሳቦችን እየሰጡ ነው፡፡ ኢሕአዴግ የማልፈታው ችግር የለም ብሎ ያምናል፡፡ የጊዜ ጉዳይ ነው እፈታዋለሁ፣ ዕድሜ ልኬን ችግር ስፈታ ነው የመጣሁት እያለ ነው፡፡ ተቃዋሚው ደግሞ በ25 ዓመታት ውስጥ መልካም አስተዳደር መስጠት ካልቻላችሁ፣ ሙስናን መቆጣጠር ካቃታችሁ ስንት ጊዜ ነው ተጨማሪ ጊዜ እንድሰጣችሁ የምትፈልጉት ይላል፡፡ ይኼ ስሜት የሚሰጥ ነገር ስላልሆነ የሚያረጋግጠው እናንተ እንደማትችሉ ነው ይላል፡፡ መፍትሔውም የመንግሥት ከሥልጣን መውረድ እንደሆነ ያስቀምጣል፡፡ የሽግግር መንግሥት ይመስረት እስከመባል ተደርሷል፡፡
ሪፖርተር፡- ኢሕአዴግ ከ15 ዓመታት በፊት ሙስናና ኪራይ ሰብሳቢነት፣ የሰብዓዊ መብትና የዴሞክራሲ አያያዝ፣ እንዲሁም የትምክህተኝነትና የጠባብነት አመለካከት ቁልፍ ችግሮች መሆናቸውን ለይቼ በመሥራቴ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ተጨባጭ ለውጥ አምጥቻለሁ ይላል፡፡ በሌላ በኩል አሁን ለተፈጠረው ችግር ዋነኞቹ ምክንያቶች እነዚሁ አጀንዳዎች ናቸው እያለ ነው፡፡ ተቺዎች እነዚህ ገለጻዎች የሚጋጩ ናቸው ይላሉ፡፡ ኢሕአዴግ ግን ለውጥ ባመጣም በቂ ስላልሆነ አጠናክሬ እመለስበታለሁ እያለ ነው፡፡ የእርስዎ እይታ ምንድነው? 
አቶ ሙሉጌታ፡- እንደኔ አመለካከት ኢሕአዴግን ለመተቸት ማስረጃ ፍለጋ ብዙ አትቸገርም፡፡ ምክንያቱም መንግሥት ራሱ የሚሰጥህ ማስረጃ ያልተለመደ ነው፡፡ በአንድ በኩል መንግሥት ደፋር ነው፡፡ ሌላ አገር ትንሽ ጥፋትን የመቀበል ነገር እንኳን አታይም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በጥቅምት ወር 2008 ዓ.ም. ባለሥልጣኖቻቸውን ሰብስበው ሲናገሩ ሕዝቡ በመልካም አስተዳደር ዕጦት መማረሩን አምነዋል፡፡ በዕለቱ የቀበረው ጥናትም ይህንኑ ነው ያረጋገጠው፡፡ መልካም አስተዳደር አላሰፈንኩም ካልክ በሥልጣን መቀጠል አመክኖአዊ አይደለም፡፡ ምክንያቱም የመንግሥት ሥራ ማስተዳደር ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ነኝ ለሚል መንግሥት ራሱን ለማረጋገጥ 25 ዓመታት እንዴት አይበቁም? ተጨማሪ ጊዜ ቢሰጠውስ ውጤታማ እንደሚሆን ማረጋገጫችን ምንድነው? ኢሕአዴግ እመኑኝ እያለ ነው፡፡ በቅርቡ በኢቢሲ የቀረቡት የኢሕአዴግ አንጋፋ አመራሮች አቶ ዓባይ ፀሐዬ፣ አቶ በረከት ስምኦን፣ አቶ አባዱላ ገመዳና ዶ/ር ካሱ ኢላላ በጋዜጠኛው ከ15 ዓመታት በፊት ታድሰናል ብላችሏል፡፡ እንዴት ነው ታዲያ አሁን መልሳችሁ እንታደሳለን የምትሉት ተብለው ሲጠየቁ አቶ አባዱላ ታዲያ ያኔ እኮ ተሃድሶ እናደርጋለን ስንል ሁለተኛ አንበሰብስም አላልንም ብለው መልሰዋል፡፡ በጣም የገረመኝ መልስ ነው፡፡ ይኼ መንግሥት የመበስበስ መብት እንደሌለው እንኳን አያውቅም፡፡ መበስበስን እንደ መብታቸው ነው የሚቆጥሩት፡፡ ሕገ መንግሥቱ መንግሥት እንድበሰብስ አይፈቅድም፡፡ በሕገ መነግሥቱ የተሰጠውን ኃላፊነት መወጣት ካልቻለ ሕዝቡ መንግሥትን የማውረድ ሥልጣን እንዳለው ይገልጻል፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ጥልቅ ናቸው፡፡ ባለሥልጣን ስለቀየርን የሚጠፉ ዓይነት አይደሉም፡፡ የመልካም አስተዳደር ችግር የፖሊሲ ችግር ነው፣ የሕግ ጥያቄ ችግር ነው፣ የፖለቲካ ጥያቄ ችግር ነው፣ የማኅበራዊ ጥያቄ ችግር ነው፡፡ የሚመጡት አዳዲስ ሰዎች ወዳለው ሥርዓት ነው የሚገቡት፡፡ ስለዚህ ሥርዓቱ ካልተቀየረ እጃቸው ይያዛል፡፡
ሪፖርተር፡- በአንድ በኩል የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አለ፡፡ በሌላ በኩል ግንባሩን የመሠረቱት ሕወሓትና ብአዴን (ኢሕዴን) የሶሻሊዝም አቀንቃኝ ነበሩ፡፡ ኢሕአዴግም በይፋ የሚከተለው ርዕዮተ ዓለም አብዮታዊ ዴሞክራሲና ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዚሁ ላይ የተጨመረው ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ሞዴል ግራ ዘመም ናቸው፡፡ ሊበራል አተያይ ያለውን ሕገ መንግሥት ግራ ዘመም በሆነው ኢሕአዴግ እንዲተረጎም መጠበቅ አይቻልም የሚሉ አሉ፡፡ ሕገ መንግሥቱን ያስተምሩ ነበርና በዚህ ይስማማሉ? 
አቶ ሙሉጌታ፡- አዎ እስማማለሁ፡፡ መንግሥት ለሕገ መንግሥቱ ምንም ደንታ ያለው አይመስለኝም፡፡ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት ራሱ የጻፈውን ሕገ መንግሥት እንደሚያከብር ምንም ማስረጃ የለኝም፡፡ የመናገር ነፃነት በሕገ መንግሥቱ ዕውቅና ተሰጥቶታል፡፡ የመናገርና የማሰብ ነፃነት ለሁሉም ነፃነቶች መሠረት ነው ብለው ከሚያስቡ ፈላስፎች ጋር እስማማለሁ፡፡ ካላሰብክ፣ ካልተናገርክ ዴሞክራሲ ብሎ ነገር የለም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን የፕሬስ ይዞታ ምን ይመስላል? ጋዜጠኛ ሽብርተኛ እየተባለ ይታሰራል፡፡ የፀረ-ሽብርተኝነት ሕጉ ዛቻን ሁሉ በሞት የሚቀጣ ነው፡፡ ተናደው የሚጽፉት ሁሉ ሽብር ተብሎ ጋዜጠኞች ይታሰራሉ፡፡ ስለዚህ ፕሬስ መንግሥት ላይ ቁጥጥር የምታደርግበትና መረጃ የምታሰባስብበት ዘርፍ መሆን አልቻለም፡፡ ሰው መሰብሰብ አይችልም፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶችም መሰብሰብ አይችሉም፡፡ ሆቴል ተከራይተው ስብሰባ ሊገቡ ሲሉ ባለቤቶቹ ላይ ጫና ተደርጎ ስብሰባ የሚበተንበት አገር ነው፡፡ ሰው ካልተሰበሰበ፣ በነፃነት ካልተናገረ፣ ሰዎች ካልተደራጁ መንግሥት ላይ ቁጥጥር ማድረግ አይቻልም፡፡ ሕገ መንግሥቱ በዋነኛነት የተሠራው የመንግሥት ሥልጣን ላይ ቁጥጥር ለማድረግ ነው፡፡ የኢሕአዴግ ሥልጣን ላይ ግን ገደብ የለም፡፡ የሽግግሩ ቻርተር ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን ዕውቅና ሲሰጥ ያለምንም ዓይነት ገደብ የተረጋገጠ መብት እንደሆነ ይገልጽ ነበር፡፡ ያኔ በነበረው የፖለቲካ ሁኔታ በተቻለ መጠን ሁሉም ኃይሎች ሊቀበሉት የሚችሉት ነገርና የውጭ ኃይሎችንም ይሁንታ ያገኘ፣ ከጊዜው ጋር መሄድ የሚችል ሰነድ ለመስጠት ኢሕአዴግ ፍላጎት ነበረው፡፡ ውስጣቸው ግን ይህን የሚፈልግና የተቀየረ አልነበረም፡፡
ኢሕአዴጎች ሕገ መንግሥቱን ከልባቸው እንዳልተቀበሉት ማረጋገጫው እስካሁን ድረስ ያላከበሩት መሆኑ ነው፡፡ አሁን አገር እንዲህ እየተናጠች በኢቢሲ ከመንግሥት የተለየ ሐሳብ ያላቸው ሰዎች አይቀርቡም፡፡ የሕዝቡ ሚዲያ ግን የሕዝቡን ሐሳብ ማስተናገድ ነበረበት፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብን ሐሳብ መንግሥት ብቻ ሊወክለው አይችልም፡፡ መንግሥት እኔ ብቻ ነኝ የሕዝብ ወኪል ካለ ዴሞክራሲያዊ ነኝ የሚለውን አባባል ማቆም አለበት፡፡ ኢትዮጵያ የብዙኃን አገር ነች ከተባለ ብዝኃነት ያለውን ሐሳብ ትጠብቃለህ፡፡ አሁን መንግሥት እያለ ያለው የኢትዮጵያን ችግር መፍታት የምችለው እኔ ብቻ ስለሆንኩ ሥልጣን ላይ መቆየት አለብኝ ነው፡፡ ከእሱ በሐሳብ የተለዩ አካላትን መጨመር አይፈልግም፡፡ አንድ ፓርቲ መላው አገሪቱን ተቆጣጥሯል፡፡ በመንግሥትና በፓርቲ መካከል ደግሞ ምንም ዓይነት ልዩነት የለም፡፡ የአውራ ፓርቲ ሥርዓት ተፈጥሯል ተብሏል፡፡ እሱን ወደ ዴሞክራሲያዊ ልማታዊ መንግሥት የማሸጋገር ሙከራም አለ፡፡ በነገራችን ላይ ልማታዊ መንግሥት በአቶ መለስ የተገለጸበትና መንግሥት በሚያወራው መካከል ሰፊ ልዩነት ነው ያለው፡፡ አቶ መለስ የግል ዘርፉ ልማቱን የሚመራና የልማት ጥምረት አካል መሆን አይችልም ነው የሚሉት፡፡ መንግሥት አሁን የሚለው የግል ዘርፉን እናበረታታለን ነው፡፡ ልማታዊ መንግሥት ዴሞክራሲያዊ መሆን ይችላል ወይ ሲባል፣ አቶ መለስ ዴሞክራሲያዊ መሆን ይችላል ብለው በግልጽ ተናግረው አያውቁም፡፡ “Dead Ends and New Beginnings” በሚለው ጽሑፋቸው አቶ መለስ ገበሬው እስኪሸጋገር ድረስ ለረጅም ጊዜ ባልተቋረጠ መልኩ ሥልጣን ላይ የሚቆይ መንግሥት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ይኼ ሙሉ በሙሉ ዴሞክራሲያዊ ያልሆነ ሐሳብ ነው፡፡
አሁን ግን ፕሮፖጋንዳው ተቀይሯል፡፡ ዴሞክራሲያዊ ነን ይባላል፡፡ ዴሞክራሲን የተቀበለ መንግሥት በተግባር ብዝኃነትን መቀበል አለበት፡፡ ይህን የተቀበለ መንግሥት ተቺና ተቃዋሚዎችን መጨቆን የለበትም፡፡ ሕጋዊና ሰላማዊ የሆኑ ተቃውሞዎችን መቀበል ግዴታ ነው፡፡ አቶ በረከት ስምኦን በቅርቡ በግልጽ የተቃውሞ ሠልፎችን እየከለከልን ነው ብለዋል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ተግባራዊ አልሆነም ብቻ ሳይሆን በዲዛይን የሚፈልገውን ነገር ለመፈጸም ዋነኛ መሣሪያ ሆኖ ለኢሕአዴግ እያገለገለ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ከፍ ያለ ደረጃ ያለው ነው፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ እንዲህ ዓይነት ሕገ መንግሥት አላት እንዲባል ብቻ የተቀመጠ ነው፡፡ የወንጀል ሕግ ውስጥ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት መናድ የሚባል ወንጀል ተደንግጓል፡፡ እኔ ምን ማለት እንደሆነ አላውቅም፡፡ ጋዜጠኞች ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመናድ ሲቀሰቅሱና ሲያነሳሱ ነበር ተብለው ሲከሰሱ ታያለህ፡፡ አንድ ግለሰብ እንዴት አድርጎ ነው ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ሊያፈርስ የሚችለው? ሕገ መንግሥቱ በአጠቃላይ ማስፈራሪያ ሆኗል፡፡ ድሮ ሕገ መነግሥቱ ጥሩ ነው ሲባል ተቃዋሚ ፓርቲዎች አይቀበሉም ነበር፡፡ የወያኔ ሕገ መንግሥት እኮ ነው የሚል መከራከሪያ ያቀርባሉ፡፡ የማንስ ቢሆን ከየትስ ቢመጣ? ዋናው ተቀባይነት ያለው ይዘት መሆኑ ነው፡፡ አሁን ነገሮች ተቀይረው ተቃዋሚዎች ሕገ መንግሥቱ ተጥሷል ሲሉ መንግሥት አልጣስኩም እያለ ነው፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ቢገነባማ ኖሮ ዜጎች በሕገ መንግሥቱ ላይ የተረጋገጠው መብታቸው ይከበርላቸው ነበር፡፡
ሪፖርተር፡- የኢሕአዴግ ከፍተኛ አመራሮች አሁንም ራሳቸውን የሚገልጹት ለሕዝቡ ጥቅም መስዋዕትነት እንደሚከፍሉ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ ተቋማትም በኢትዮጵያ ደረጃ ከሚገኙ አገሮች አንፃር በአገሪቱ ያለው የሙስና ደረጃ ዝቅተኛ ነው ይላሉ፡፡ የሕዝቡ አመለካከት ግን እነዚህ አመራሮች በከፍተኛ ሙስና መዘፈቃቸውን አመላካች ነው፡፡ የእርስዎ ግምገማ የቱ ላይ ያርፋሉ? 
አቶ ሙሉጌታ፡- የኢሕአዴግ አመራሮች ወደ ትጥቅ ትግል ሲገቡ ልጆች ነበሩ፡፡ በአብዛኛው 20 እና ከዚያ በታች ዕድሜ ላይ ነበሩ፡፡ ያመኑበትን ለመፈጸም ነው የሄዱት፡፡ በወቅቱ በነበረው የፖለቲካ ሁኔታና ርዕዮተ ዓለም ነፃ አውጭነት ይገባኛል፡፡ መንግሥት ከሆኑ በኋላ ግን ሙሉ በሙሉ ተለውጠዋል፡፡ የአመራር ሪከርዳቸው ችግር አለበት፡፡ እኔ የኢትዮጵያን ሙስና የማወዳድረው ከኡጋንዳ ወይም ከናይጄሪያ ጋር አይደለም፡፡ ከሌላ አገር ጋር ማወዳደር ያሳስታል፡፡ መጀመሪያ በራሳችን መሥፈርት ነው መገምገም ያለብን፡፡ በኢትዮጵያ ሙስና በቁጥርም ሆነ በጥራት እየጨመረ ነው ወይስ እየቀነሰ? መንግሥትስ ሙስናን አደጋ በማያመጣ መልኩ ተቆጣጥሮታል? ወይስ ከመንግሥት ቁጥጥር ውጪ ሆኗል? የውጭ ተቋማትን ሪፖርት ተወው፡፡ ራሱ ኢሕእዴግ በባህር ዳር ባደረገው ጉባዔው የህልውና ሥጋት ነው ብሎታል፡፡ አይጨምርም፣ እንቆጣጠረዋለን ብላችሁ ቃል ገብታችሁ ለምን ጨመረ ብለን መጠየቅ አለብን፡፡ እኔ የኢሕአዴግ ባለሥልጣናትን ሐሳብ አልቃወምም፡፡ የኢሕአዴግ ባለሥልጣናት ምን እንደሚያስቡ ስለማላውቅ ለዚህ አገር መጥፎ ያስባሉ ማለት አልችልም፡፡ እኔ የምፈርደው በድርጊታቸው ነው፡፡ አገሪቱን በአግባቡ እያስተዳደሩ እንዳልሆነ ራሳቸው አምነዋል፡፡ በአግባቡ ለማስተዳደር ዕርምጃዎች እንወስዳለን ነው ያሉት፡፡ ለምሳሌ በመካከላቸው ያሉ ሥልጣንን ለግል ጥቅማቸው የሚያውሉትን እንመነጥራለን ብለዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በቅርቡ በአማራና በትግራይ ክልል መካከል ወልቃይትን አስመልክቶ ለተፈጠረው ችግር ተጠያቂዎቹ የአማራና የትግራይ መሪዎች ናቸው ብለዋል፡፡ የትግራይ መሪ አቶ ዓባይ ወልዱ ናቸው፡፡ የአማራ መሪ ደግሞ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ናቸው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሁለት ሰዎች ናቸው ያጠፉት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን እንዳጠፉ አምነው ተቀብለዋል፣ ችግሩንም ራሳቸው ያስተካክሉታል ብለዋል፡፡ በችግሩ ሳቢያ የሰው ሕይወት ጠፍቷል፣ ንብረት ወድሟል፡፡ አጥፍቻለሁ ያለ ሰው እንኳን የማይጠየቅ ከሆነ ኢሕአዴግ ከልቡ ዕርምጃ አይወስድም ማለት ነው፡፡ ቀውስ እንዳለ ከተቀበሉ በኋላ ራሱ በአግባቡ እየመሩ አይደለም፡፡ ስለዚህ ወሬውና እውነታው በጣም የተለያየ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በአገሪቱ እየታዩ ካሉት ተቃውሞዎች አንፃር ኢሕአዴግ ሥልጣን ይልቀቅ የሚሉ አሉ፡፡ በሌላ በኩል ኢሕአዴግ ሥልጣን ቢለቅ የሚረከብና የሚያስተዳድር ዝግጁ የሆነ ጠንካራ ተቃዋሚ ስለሌለ ገዢው ፓርቲ መሠረታዊ ማሻሻያ አድርጎ እንዲቀጥል የሚፈልጉም አሉ፡፡ ወቅቱ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ላይ በጥልቀት ለመወያየት የሚያስገድድ ነውና አንድ መሠረታዊ ጥያቄ ላንሳ፡፡ ኢሕአዴግ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሁሉንም ነገር አፍርሰው እንደ አዲስ የመገንባት ዕቅድ ስላላቸው እንደ ሥጋት እወስዳቸዋለሁ፣ የጀመርኩትን ለውጥ ማስቀጠል ቢፈልጉ አብሬያቸው እሠራ ነበር ይላል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ደግሞ የሕዝብ ይሁንታ ያገኘ ፓርቲ ምንም ይሁን ዕቅዱ ሥልጣን መያዝ እንዲችል መብቱን ያረጋግጣል፡፡ ሁለቱን ነገሮች እንዴት ማስታረቅ ይቻላል? 
አቶ ሙሉጌታ፡- ከመሠረቱ መንግሥት ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ያጠናክር የሚለው ነገር በኢሕአዴግም ሆነ በተቃዋሚዎች ሲወራ ገብቶኝ አያውቅም፡፡ መንግሥት ተቃዋሚዎችን የማጠናከር ግዴታ የለበትም፡፡ ተቃዋሚዎችም በመንግሥት የመረዳት መብት የላቸውም፡፡ እኔ ከመንግሥት የምጠብቀው ሕገ መንግሥቱን ተግባራዊ እንዲያደርግ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ ተግባራዊ ከሆነ ተቃዋሚዎች የመንግሥት ድጋፍ አያስፈልጋቸውም፡፡ የሕግ ድጋፍ ነው የሚያስፈልጋቸው፡፡ የሕግ የበላይነት ካለ ተቃዋሚዎች ዕድል ያገኛሉ፡፡ ነፃ የሐሳብ ገበያው ላይ የፖለቲካ ፉክክር ይኖራል፡፡ አሁን መንግሥት እንደ አባትና ችሮታ አከፋፋይ ነው ራሱን እያየ ያለው፡፡ ተቃዋሚዎች የተዳከሙት መንግሥት ስለማይረዳቸው ሳይሆን ስለሚጨቁናቸው ነው፡፡ ሕጉ የሚፈቅድላቸውን ነፃነት እንዳይጠቀሙ አድርጓል፡፡ እርግጥ ነው በተቃዋሚ ፓርቲዎችም በኩል ከሐሳብ ግልጽነት አንፃር ጉድለት አለ፡፡ ምን ያህሎቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሕገ መንግሥቱ እንደገባቸው እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ በአገሪቱ የሚታየው የጥላቻ ፖለቲካ ነው፡፡ መንግሥት ተቃዋሚዎቹ አገር አጥፊዎች ናቸው ብሎ ነው የሚያስበው፡፡ በተመሳሳይ ተቃዋሚዎቹ መንግሥት አገር አጥፊ ነው ብለው ነው የሚያስቡት፡፡ አንዱ የአንዱን ጥፋት ነው የሚፈልገው፡፡ ሁለቱም ሙሉ በሙሉ ፀረ ዴሞክራሲያዊ ናቸው፡፡ የጥላቻና የመጠፋፋት ፖለቲካ የዴሞክራሲ ፍልስፍና አካል አይደለም፡፡ ሁለቱም በጥላቻ ታውረዋል፡፡ ሁለቱም ጠባብ ፍላጎት ነው ያላቸው፡፡ መሆን ያለበት ሁለቱም ዕውቅና ተሰጣጥተው መሥራት ነው፡፡ ሁለቱም ሕገ መንግሥቱን ተቀብለው ክርክራቸውን እሱ ላይ መሠረት ቢያደርጉ ተመራጭ ነበር፡፡ መንግሥትም ተቃዋሚ ፓርቲ አስፈላጊ መሆኑን ቢቀበል ጠቃሚ ነው፡፡ ተቃዋሚ የሌለው ዴሞክራሲ የለም፡፡ የሐሳብና የድርጅቶችን ብዝኃነት መቀበል አለበት፡፡
ተቃዋሚዎችም መንግሥት አስፈላጊ መሆኑን ተቀብለው ሥልጣን ለመያዝ ውድድር ውስጥ ለመግባት ዝግጁ መሆን አለባቸው፡፡ ይኼ ለችግሮች መፍትሔ ለመሻት መነሻ መሆን ይችል ነበር፡፡ ነገር ግን መንግሥት አሁን አገሪቱ ያለችበትን ችግር ጥልቀትና አስቸኳይነት የገባው አልመሰለኝም፡፡ ይኼ ነገር እንደ ንፋስ የሚያልፍ ሊሆን ይችላል፡፡ የሚያልፍ ባይሆንስ? ትልቅ አደጋ የሚፈጥር ቢሆንስ? አሁን የብሔር ውጥረቱ እያየለ ነው፡፡ ይኼ ነገር እየተባባሰ መጥቶ መንግሥት ጣልቃ ሳይገባ ከተወው ድንገት ወደ ሌላ ደረጃ ሊደርስ ይችላል፡፡ መደራጀት የሚፈለጉ የተለየ ሐሳብ ያላቸው ሰዎች አሉ፡፡ ኢሕአዴግ የአስተሳሰብ ለውጥ ያስፈልጋል ይልሃል፡፡ ምንም ዓይነት የአስተሳሰብ ለውጥ ያላሳየ ድርጅት ቢኖር ኢሕአዴግ ነው፡፡ በአንድ በኩል እኔ የማልፈታው ምንም ዓይነት ችግር የለም ይላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የመልካም አስተዳደር ችግርን መቅረፍ አልቻልኩም ይላል፡፡ መልካም አስተዳደር አለማስፈን ችግር አይደለም እንዴ? ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚፈልጉት ይኼ መንግሥት እንዲወርድ ነው፡፡ እኔም እኮ ማስተዳደር ያልቻለ ኃይል መቀጠል የለበትም በሚለው አመክንዮ እስማማለሁ፡፡ ነገር ግን የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ ምን ይመስላል ብለን መጠየቅ አለብን፡፡ አንደኛ ኢሕአዴግን እንዴት ነው የምታወርደው? ውረድ ስትለው አልወርድም ቢልህ በምን ታስገድደዋለህ? መዓት ጊዜ ውረድ ተብሎ አልወርድም ብሏል፡፡ ስለዚህ ውጊያ ውስጥ ትገባለህ ማለት ነው፡፡ እሱም ቢሆን እየተሞከረ ነው፡፡ ውጊያና ጭፍጭፍ ወደምንፈልገው የተሻለ ሕይወት ሊመራን አይችልም፡፡ ስለዚህ የማሻሻያ ዕርምጃዎች ያስፈልጋሉ፡፡ መጀመሪያ መንግሥት የማሻሻያ ሒደቱ አካል መሆን እንዳለበት ማንም ሰው ዕውቅና ሊሰጠው ይገባል፡፡ ተቃዋሚው ኢሕአዴግን የማይጨምር ማሻሻያ አመጣለሁ ማለቱ አደጋ አለው፡፡ ኢሕአዴግ ኃይለኛ ድርጅት፣ ጠንከራ ጦርና የፀጥታ ኃይል አለው፡፡ እንኳን በአገር ውስጥ በዓለም ደረጃ ቀላል መንግሥት አይደለም፡፡ ኢሕአዴግ ሥልጣን የያዘው ተዋግቶ ነው፡፡ ስለዚህ ስለጠየቅካቸው ሥልጣን አይሰጡህም፡፡ ኢሕአዴጎች ችግሩ ገብቷቸው መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት ቢያምኑ መልካም ነው፡፡ በዚህ ካላመኑ ግን አደገኛ ሁኔታ ነው የሚፈጠረው፡፡
በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ያለው የተቃውሞ እንቅስቃሴ ወደ ትግራይ፣ አፋር፣ ሶማሌ ከተጀመረ ሁሉንም በመጨቆን አይዘልቅም፡፡ ሠራዊቱም ይደክመዋል፡፡ ስለዚህ መጠነ ሰፊ ብጥብጥ ሊፈጠር ይችላል፡፡ የት እንደሚቆምና ምን ዓይነት መልክ እንደሚኖርው ሁሉ መገመት አትችልም፡፡ መንግሥት ሁሉን አቀፍ የማሻሻያ ፕሮግራም አከናውናለሁ፣ ሕገ መንግሥቱን ተግባራዊ አደርጋለሁ ሊል ይችላል፡፡ ነገር ግን ችግሩ እስኪረጋጋ አጋጣሚውን ለማለፍ ሊያውለውም ይችላል፡፡ ሸውዶ ለማለፍ ሊያስብ ይችላል፡፡ ዘላቂ መፍትሔ የሚገኘው ኢሕአዴግ ከልቡ አምኖ መሠረታዊ ማሻሻያ ሲያደርግ ነው፡፡ ማሻሻያው ሕገ መንግሥቱን ተግባራዊ ከማድረግ ይጀምራል፡፡ ይህ ማለት ሕዝብ በነፃነት ይናገራል፣ ይሰባሰባል፣ ሠልፍ ይወጣል፣ ይደራጃል፡፡ እስከ ቀጣዩ ምርጫ ባሉት ዓመታት ለውጥ ማምጣት ይቻላል፡፡ እነዚህን ጨቋኝ የሚባሉ ሕጎችም ዛሬ መሻር ይቻላል፡፡ አስቻይ የሆኑ ሌሎች ሕጎችን ማውጣት ይቻላል፡፡ ይኼ መንግሥት ለዘለዓለም ሊቀጥል እንደማይችል ማወቅ አለበት፡፡ አንድ ቀን ማለፍ አለበት፡፡ ሽግግሩ የተሳለጠ እንዲሆን መዘጋጀት አለብን፡፡ ሁሉንም ዴሞክራሲያዊ መብቶች ዛሬ ተግባራዊ እናድርግ ብትል ብጥብጥና ግርግር ይፈጠር ይሆናል፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ ችግር በአገር ውስጥ ብቻ የተገደበ አይደለም፡፡ ሰው በነፃነት መተንፈስ ሲጀምር ለየት ያሉ አዳዲስ ሐሳቦችም ይመጣሉ፡፡ የመንግሥት ሚዲያ ክፍት ሆኖ ሐሳቦች በነፃነት ከተንሸራሸሩ ቤት ውስጥ ተቀምጠው የነበሩ የተደበቁ ሐሳቦች ይወጣሉ፡፡ በእነዚህ ሐሳቦች ላይ የሚደረገው ውይይትና ክርክር ወደ ተሻለ ደረጃ ይወስደናል፡፡
ሪፖርተር፡- ከላይ በጠቀሱት የአራቱ የኢሕአዴግ አንጋፋ መሪዎች ውይይት ወቅት አቶ በረከት ስምኦን በሥራ ላይ ያለው የምርጫ ሕግ ከሚሠራበት የአብላጫ ድምፅ አሠራር ይልቅ፣ የተመጣጣኝ ውክልና አሠራር ብዝኃነት ላላቸው እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገሮች የተሻለ ነው በሚል የሚቀርበውን ሐሳብ መንግሥት እያጤነው እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡ ይኼ ማሻሻያ ከሌሎች መሰል የማሻሻያ ሐሳቦች ጋር ተግባራዊ ቢደረግ ትልቅ ለውጥ ያመጣል ብለው ያስባሉ? 
አቶ ሙሉጌታ፡- እኔ ይኼ የቅንጦት ጥያቄ ነው ብዬ ነው የማስበው፡፡ ይኼ ጥያቄ ታሳቢ የሚያደርገው ኢትዮጵያ ውስጥ ፍትሐዊና ነፃ የሆነ ምርጫ ሲካሄድ ቆይቷል የሚል ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ፍትሐዊና ነፃ የሆነ ምርጫ ተካሂዷል ብዬ አላስብም፡፡ ስለዚህ ፍትሐዊና ነፃ የሆነ ምርጫ ባልተካሄደበት ሁኔታ ምን ዓይነት የምርጫ ሥርዓት እንከተል? አሸናፊው እንዴት ይለይ? ፓርላማው እንዴት ይደራጅ? የሚሉት ጥያቄዎች ሁለተኛ ቦታ የሚሰጣቸው ነው የሚሆኑት፡፡ ፍትሐዊና ነፃ የሆነ ምርጫ ተደርጎ ቢሆን ኖሮ አሁን በሥራ ላይ ያለው የምርጫ ሥርዓት መጥፎ አይደለም፡፡ ዴሞክራሲ ማለት የአብዛኛው ውሳኔ ነው፡፡ ስለዚህ የአብላጫ ድምፅ አሠራር ችግር አይደለም፡፡ ተመርጬ ነው ሥልጣን የያዝኩት የሚለው የኢሕአዴግ ተደጋጋሚ ፕሮፓጋንዳ የሠራ ይመስለኛል፡፡ ነገር ግን አንተን ብቻ መቶ በመቶ የመረጠ ሕዝብ በዚህ መጠን እንዴት ይቃወምሃል? ይኼ ሁሉ ጥላቻ ከየት መጣ? ስለዚህ ያልተመለሱ ድፍረት የሚጠይቁ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ እንዳሉት በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ መንግሥት አለ ካልክ የትኛው የምርጫ ሥርዓት ይሻላል የሚለው ትርጉም ይኖረዋል፡፡ ለእኔ ግን ዋናው ነገር ይኼ አይደለም፡፡
ሪፖርተር፡- ሕገ መንግሥቱ ተግባራዊ ይደረግ ከማለት ይልቅ ማሻሻያ እንዲደረግበት ወይም በሌላ ሕገ መንግሥት ይቀየር በማለት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ቅድሚያውን ይያዙ እንጂ ምሁራን፣ ሲቪል ማኅበራትና የሙያ ማኅበራትም ተመሳሳይ ሐሳብ ሲሰነዝሩ ይታያል፡፡ ይህ አዝማሚያ መንግሥት በሕገ መንግሥቱ መሠረት እንዲያስተዳድር ጫና እንዳያደርጉ ገድቧቸዋል የሚለውን ትችት ይቀበሉታል?
አቶ ሙሉጌታ፡- ይኼ የሚመነጨው አንዱ ስለአንዱ ካለው አመለካከት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት በመሠረቱ የሊበራል ፍልስፍና መሠረት ነው ያለው፡፡ የአሜሪካ ሕገ መንግሥት ገና ሳይፀድቅ አሥር ማሻሻያዎች ተደርገዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት የማሻሻያ አንቀጽ አለው፡፡ ተግባራዊ ለማድረግ አስቸጋሪ ሊሆን ቢችልም የማይቻል ግን አይደለም፡፡ ይኼ ሕገ መንግሥት ኢሕአዴጎች ስለጻፉት ወይም ስላፀደቁት መጥፎ ነው ማለት አይደለም፡፡ መገምገም አለበት፡፡ መቀየር ይችላል፡፡ ልታስወግደውም ትችላለህ፡፡ በሰዎች የተሠራ በመሆኑ መለኮታዊ ባህሪ የለውም፡፡ ነገር ግን ጥሩ መነሻ መሆን የሚችል ነው፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከፍ ያለ የሞራል ልዕልና የሚኖራቸው በሕገ መንግሥቱ መከራከር ሲችሉ ነው፡፡ ሌሎቹ አማራጮች በጣም አደገኛ በመሆናቸው ሕገ መንግሥቱን ተግባራዊ ማድረግ ቅድሚያ ቢሞከር ጥሩ ነው እላለሁ፡፡ ሰላማዊ ሽግግር ስለማድረግ ሲታሰብ የመንግሥትን ፍርኃት አብሮ ማገናዘብ ያስፈልጋል፡፡ ከሥልጣን መውረድ ቀላል አይደለም፡፡ መጠየቅን ያመጣል፡፡ እንደምትጠየቅ ካወቅክ ሥልጣን ለመልቀቅ ትንገታገታለህ፡፡ በሰላም የሚኖሩበትን ሁኔታ ከማመቻቸት ጀምሮ በወንጀል የማይጠየቁበትን መተማመኛ እስከመስጠት የሚያደርስ ዕርምጃ መውሰድ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል፡፡
ሪፖርተር፡- በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ከተከሰቱ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች ከተለዩ ጥያቄዎች መካከል አንዱ ፍትሐዊ የሀብትና የሥልጣን ክፍፍል እየተደረገ አይደለም የሚለው ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱና የፌዴራል ሥርዓቱ ሲቀረፁ ታሳቢ ያደረጉት ይህን በየተዋረዱ ባሉ አስተዳደሮች ማስቻል ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ሕገ መንግሥቱ ላለፉት 21 ዓመታት ሥራ ላይ ከዋለ በኋላ ይኼ ጥያቄ መቅረቡን እንዴት አዩት?
አቶ ሙሉጌታ፡- ይኼ ከላይ የገለጽኩትን ሐሳብ የሚያጠናክር ነው፡፡ ምክንያቱም ሕገ መንግሥቱ ተግባራዊ ቢሆን ኖሮ ይኼ ጥያቄ አይነሳም ነበር፡፡ ሕገ መንግሥቱ እነዚህ ጥያቄዎች ሲነሱ ምላሽ የሚሰጥበትን ሥርዓት ዘርግቷል፡፡ ተግባራዊ ቢሆን ኖሮ 21 ዓመት ሳይጠብቅ ወዲያው ምላሽ ይሰጣቸው ነበር፡፡ በኦሮሚያ፣ በአማራና በኮንሶ ሕዝቡ ተቃውሞውን አቅርቧል፡፡ ይኼ እኮ 70 በመቶ አካባቢ የሚሆን ሕዝብ ነው፡፡ በዴሞክራሲ ውስጥ ሕዝብ ተሳስቷል አይባልም፡፡ ችግሩ ያለው ሕዝቡ ዘንድ ሳይሆን ራሱ ኢሕአዴግ ጋ ነው፡፡ ሕዝብ ታፍኗል፡፡ እስካሁንም አለማመፁ ይገርማል፡፡ የመሬት ዝርፊያ አለ፡፡ መሬታቸው ተወስዶ ሜዳ ላይ የወደቁ ኦሮሞዎች አሉ፡፡ ይኼ አንገብግቧቸው ተነስተው ቢጮኹ ምን ያስገርማል? ግን መንግሥት ጆሮ የለውም፡፡ ይህን እንዲያደርግ የሚያስገድድ የቁጥጥር ሥርዓት የለም፡፡ መንግሥት ከሕገ መንግሥቱ ሐሳብ በተቃራኒው ገደብ የለሽ ሥልጣን ነው ያለው፡፡ ማጥፋት አደጋ የለውም፡፡ ስለዚህ የሚያምፅ ሰው በጥይት ሲመታም የሚመረምር አካል የለም፡፡ ዕርምጃው ተመጣጣኝ ስለመሆኑ ወይም አለመሆኑ ልናውቅ አንችልም፡፡ ተጠያቂነት የሌለበት ሥርዓት ነው የፈጠርነው፡፡ መንግሥት ሕዝቡ ብሶቱን በነፃነት፣ በየቦታው፣ በተለያዩ መድረኮች የሚገልጽበትን የማይፈጥር ከሆነ ውጥረቱ ወደ አደገኛ ደረጃ ሊያመራ ይችላል ብዬ እሠጋለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- በፌዴራል ደረጃ ያለው ሥልጣንና ሀብት ለክልሎች ወይም ለብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በፍትሐዊነት መከፋፈለ እንዳለበት ሕገ መንግሥቱ ታሳቢ ያደርጋል፡፡ በተቃውሞዎቹ የትግራይ ብሔር አባላት እንደ ጦር ኃይልና ደኅንነት ውስጥ ያሉትን ቁልፍ ቦታዎች ጨምሮ ተቆጣጥረውታል የሚል ወቀሳ ጎልቶ ወጥቷል፡፡ የበላይነቱ ምን ያህል እንደሆነ በዳታና በማስረጃ ባይቀርብም አመለካከቱ ያላቸው ሰዎች በርካቶች ናቸው፡፡ መንግሥትም ጥያቄው ሲቀርብለት መርህ በመናገር ሲያልፈው ይታያል፡፡ ይህ በትግራይ ተወላጆች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ ያለ ጥያቄ ላይ ምን አስተያየት አለዎት?
አቶ ሙሉጌታ፡- ስለጥያቄው አግባብነት መረጃ የለኝም፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ የሥልጣን ክፍፍል እንዴት ነው የሚለካው? እሱ አጠያያቂ ሊሆን ይችላል፡፡ ሀብትስ እንዴት ነው የሚከፋፈለው? እነዚህ ጉዳዮች ላይ ስትስማማ ቆጠራ ማድረግ ትችላለህ፡፡ በጉዳዩ ላይ አስተያየቴን ልሰጥህ እችላለሁ እንጂ የማጣቅሰው መረጃ የለኝም፡፡ ከእውነታው ይልቅ ያለው አመለካከት ወሳኝ ነው፡፡ ያለው አመለካከት ሕወሓት የበላይነት የያዘበት መንግሥት ነው ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የሚል ነው፡፡ ሁለተኛ ሕወሓት የበላይነት ስለያዘ ትግሬዎች ተጠቃሚዎች ናቸው የሚል አመለካከትም አለ፡፡ ትግሬዎች ደግሞ ከአጠቃላይ የሕዝብ ብዛት ውስጥ ስድስት በመቶ ነው ድርሻቸው፡፡ አመለካከቱ እውነት ከሆነ ስድስት ሚሊዮን ሕዝብ የተቀረው 94 ሚሊዮን ሕዝብ ላይ የበላይ መሆኑ ተቀባይነት የለውም፡፡ ትልቅ ችግርም ነው፡፡ ተቃውሞ ያቀረበው ሁሉ ትግሬ የበላይነት ይዟል ብሎ ስለማመኑ አላውቅም፡፡ በዕለት ከዕለት ሕይወቴ ግን ይህን አመለካከት ብዙ ቦታ አግኝቼዋለሁ፡፡ እኔን ትግርኛ የሚናገሩ ቤተሰቦች ናቸው የወለዱኝ፡፡ ራሴን ጨምሮ ብዙ ትግርኛ ተናጋሪዎች በዚህ እንደሚያዝኑ አውቃለሁ፡፡ ሠርቶ የሚኖር መዓት ትግሬ አለ፡፡ እርግጥ ነው በዘመድና በመሳሰለው የሚጠቀም ትግሬም አለ፡፡ ትግሬ ብቻ ሳይሆን ከመንግሥት ጋር ቅርበት ያለው ሌላውም ይጠቀማል፡፡ ተጠቃሚ የሆነው ትግሬ ቁጥር ከሌሎች ሲነፃፀር ምን ያህል ነው የሚለውን አላውቅም፡፡ ሌላው ትግሬና ሕወሓት አንድ ናቸው ብሎ የሚያምን ሰው ብዙ ነው፡፡ እኔ አንድ ናቸው ብዬ አላስብም፡፡ እንደዚያ የሚያስቡ ትግሬዎች አሉ፡፡ እንደዚያ የሚያስቡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አሉ፡፡ ይኼ ስህተት ነው፡፡ ነገር ግን ሥልጣን ገደብ ስለሌለው ጥቅሞችን ባለሥልጣናት እንደፈለጉ እንዲያከፋፍሉና ሥልጣናቸውን ያላግባቡ እንዲጠቀሙ ዕድል ፈጥሮላቸዋል፡፡ ስለዚህ የሥልጣን ቦታዎችን ስትቆጥር የሚበዙት ትግሬዎች ከሆኑ፣ ትግሬዎች ሌሎች ትግሬዎችን የመጥቀም አዝማሚያቸው ከፍ ይላል፡፡
ሪፖርተር፡- ተቃውሞዎቹ ቀዝቀዝ እያሉ ነው በተባለበት ወቅት ባለፈው ሳምንት የኢሬቻ በዓል ሲከበር ብዙ ሰዎች ተረጋግጠውና ጉድጓው ውስጥ ገብተው ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ በዓሉ የሚደረግበት ቦታና የሚገኘውን ሕዝብ ብዛት አውቆና ገምቶ መንግሥት አድርጌዋለሁ ከሚለው ጥንቃቄና ዝግጅትም በላይ ዝግጁ ቢሆን ኖሮ፣ አደጋውን ማስወገድ ይችል ነበር በሚል የሚቀርበውን ትችት እንዴት አዩት?
አቶ ሙሉጌታ፡- አሟሟታቸው በጣም የሚያሳዝን ነው፡፡ ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን የሚያሳምም ነው፡፡ ለቤተሰቦቻቸው መፅናናትን እመኛለሁ፡፡ በኢሬቻ በዓል የሞቱ ሰዎችን አስመልክቶ የተለያዩ የሚጋጩ ሪፖርቶች እየወጡ ነው፡፡ የሁነት ጥያቄዎች አሉ፡፡ መንግሥት ያደረገው ዝግጅትና ጥንቃቄ ምን ያህል እንደነበር፣ አደጋው በትክክል እንዴት እንደደረሰ ቢጣራና ምን እንደጎደለና የቱ ላይ ድክመት እንደታየ ቢረጋገጥ ጥሩ ነው፡፡ በዓሉ የተደረገበት ቦታ አካባቢ ገደላማና የደኅንነት ሥጋት የነበረበት መሆኑ አስቀድሞ ይታወቅ ነበር፡፡
ሪፖርተር፡- በአንዳንድ ሪፖርቶች የቀረበው የፀጥታ ኃይሎች የበዓሉ ተሳታፊዎች ላይ ጥይት ተኩሰዋል የሚል ክስ ማስረጃ ያልቀረበበት ቢሆንም፣ በወቅቱና በቦታው የነበረውን ተቃውሞ ለማብረድ የተተኮሰው አስለቃሽ ጭስ አስፈላጊነት ላይ ጥያቆዎች ተነስተዋል፡፡ ሰዎች በመረጋገጥና ገደል ውስጥ በመግባት እንዲሞቱ መነሻ ከመሆኑ አኳያ የአስለቃሽ ጭሱ መተኮስን አስገዳጅ ያደረገው ምን ቢፈጠር ነው የሚል ጥያቄም ቀርቧል፡፡ እርስዎ ሁኔታውን እንዴት ገመገሙት?
አቶ ሙሉጌታ፡- መንግሥት ፀጥታ የማስከበር ኃላፊነት አለበት፡፡ ፀጥታው ሲደፈርስ በአግባቡ ምላሽ አልሰጠም፡፡ ችግሩ የተፈጠረው ስላልቻለ ነው፡፡ በዚህ መንግሥት ኃላፊነት ሊወስድ ይገባል፡፡ አስለቃሽ ጭሱ ለምን ተተኮሰ? ተኳሹ በመንግሥት ታዞ ነው ወይስ ደንግጦ ነው? በዓሉ ከመጀመሪያ እስከ መጨረሻ በሰላም እንዲያልቅ የማድረግ፣ ማንም ሰው እንዳይጎዳ የመጠበቅና በሰላም ወደ ቤቱ እንዲገባ ማድረግ አጠቃላይ የመንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡ ይህን ባለማድረጉ አደጋ ተከስቷል፡፡  
ሪፖርተር፡- በዓሉ ወደ ተቃውሞ መድረክነት ተቀይሮ እንደነበር ታይቷል፡፡ መንግሥት ይህን መሰል ያልታቀዱ ተቃውሞዎች ሲከሰቱ ምን ዓይነት ዕርምጃ ነው መውሰድ ያለበት?
አቶ ሙሉጌታ፡- በዓሉን ወደተቃውሞ የቀየሩት ወጣቶች ናቸው፡፡ በጣም ተናደዋል፣ ተቆጥተዋል፡፡ ጥቂት አይደሉም፡፡ በጣም ብዙ ናቸው፡፡ ፍላጎታቸው ፖለቲካዊ ይዘት እንዳለው ግልጽ ነው፡፡ መንግሥት ግን በመግለጫው ፀረ ሰላም የሆኑ ጥቂት ልጆች ናቸው ነው ያለው፡፡ የሕግ ጥሰት ጥያቄ አድርጎ ነው ያቀረበው፡፡ ሁሌም እንደዚህ ነው የሚያደርገው፡፡ ምን ዓይነት መፍትሔ እንደሚሰጥ መገመት ይቻላል፡፡ ሰዎችን ይለያል፣ ያስራል፣ ፍርድ ቤት ይወስዳል፣ ክስ ይመሠርታል፣ ይፈረድባቸዋል፡፡ ይኼ መንግሥት ሁሌም የሚወስደው አማራጭ ነው፡፡ ሌላው አማራጭ ሰው ተቃውሞ ያሰማው በፖለቲካ ልዩነት መሆኑን መቀበል ነው፡፡ የፖለቲካውን ችግር ለመፍታት መዘጋጀት አለብህ ማለት ነው፡፡ የሕግ ጥሰት አድርገህ ከወሰድከው መሠረታዊ ችግሩን ሊፈታልህ አይችልም፡፡ መንግሥት በክህደት ዓለም ውስጥ እየኖረ እንደሆነ ብቻ ነው የሚያረጋግጠው፡፡ ሰዎች ስሜታዊ ስለሆኑ ተቃውሞውን ሊያባብሰው ይችላል፡፡ Read more here