Monday, October 10, 2016

የኢትዮጵያ የምርጫ ህግ ማሻሻያ ይደረግበታል- ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ

የኢትዮጵያ የምርጫ ህግ
የፌዴራል መንግስቱን በአዲስ መልክና ቅኝት ለማዋቀር ተግባራዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ ተናገሩ። ፕሬዝዳንቱ ይህን ያሉት የሕዝብ ተወካዮችና የፌዴሬሽን ምክር ቤት የጋራ ጉባዔ መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ነው።
መንግስት በነደፈው መሰረታዊ የለውጥ አቅጣጫ በተለይም ላለፉት 15 ዓመታት ፈጣን ዕድገት እየተመዘገበ መቆየቱን ገልጸዋል።
የአገሪቷ ሕዝቦች በሁሉም መስክ የተጀመሩ መልካም ስራዎችና አገሪቷን ከድህነት ለማውጣት የሚደረገው መፍጨርጨር ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ፍላጎት እንዳላቸውም ተናግረዋል።

“በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ፣ በዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር እንዲሁም በውስጣዊ ሠላምና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መስክም ረጅም ጉዞ  ተጉዘናል።” ነው ያሉት ፕሬዝዳንቱ።

በአገሪቷ ሕዝቦች ትግልና ጥረት የተመዘገቡ ድሎችን በማስጠበቅ መልካም ጅምሮችን ዳር በማድረስ የሕዝቡን ተጠቃሚነት በስፋት ማሳካት እንደሚገባም አመልክተዋል።

ያም ሆኖ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርካታ ችግሮች ማጋጠማቸውን፤ ችግሮቹ ከዕድገት ጋር ተያይዘው የመጡ እንዲሁም በየደረጃው የሚገኙ የመንግስት አመራር አካላት የአቅም ማነስ፣ የስነ-ምግባርና በቅንነትና በታማኝነት ህዝብን ከማገልገል ጉድለቶች የመነጩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

“የመልካም አስተዳደር ችግሮችም ሆነ የህዝባችንን ተጠቃሚነት በተገቢው ደረጃ ያለማረጋገጥ ድክመት ከእነዚህ የሚመነጩ ናቸው” ነው ያሉት።

በመንግስት የኃላፊነት ቦታዎች ላይ የተቀመጡ ሰዎች የተረከቡትን ሕዝባዊ አደራ በመዘንጋት ስልጣንን የግል መጠቀሚያ ከማድረግ አተያይ ጋር ተያይዞ ተጨባጭ ስህተቶች በመፈጸማቸው የተከሰቱ መሆኑንም አክለዋል።
በመሆኑም ኅብረተሰቡ ቅሬታቸውንና የሚታያቸውን የመፍትሄ ሃሳብ ሲያቀርቡ ቆይተዋል ነው ያሉት ፕሬዝዳንት ሙላቱ።
መንግስትም ይህን በመቀበል ባለፈው ዓመት መጨረሻ ራሱን ከዚህ ዝንባሌ ለማጽዳት ቁርጠኛ እንቅስቃሴ መጀመሩ ወደ ቀጣይ የለውጥ ሂደት ለመሸጋገር አንዱ ቁልፍ እርምጃ በመሆን ያግዛል።

“ከዚህ በመነሳት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስራውን በሚጀምርበት ወር የፌዴራል መንግስትን በአዲስ መልክና ቅኝት ለማዋቀር ተግባራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ይደረጋል” ብለዋል።
በዚህ መሰረት የመንግስትን ስልጣን ያለአግባብ የመጠቀም ዝንባሌን የሚገታና በውጤት አልባነት ስልጣን ላይ ተቀምጦ መቆየት የማይቻል መሆኑን የሚያረጋግጥ አዲስ የመንግስት ምክር ቤት የማደራጀት እንቅስቃሴ እንደሚካሄድም ተናግረዋል።
እንደ ፕሬዝዳንቱ ገለጻ በዚህ ሂደት ብቃትና ቅንነት ያላቸውን ግለሰቦች በኃላፊነት ላይ በማስቀመጥ የመንግስት የስራ አፈጻጸም በውጤትና በውጤት ብቻ የሚመራ እንዲሆን መደረግ ይጀምራል።
ሠላም ለማወክ የሚሹ ጸረ-ሠላምና አሸባሪ ኃይሎችን በመመከትና የተከሰቱ ችግሮችን በአስተማማኝ በመፍታት በሁሉም መስክ ሚዛኑን የጠበቀ ሕገ-መንግስታዊ ስርዓት በተከተለ መልኩ የሚካሄድ ትግል መጠናከር እንደሚገባውም ጠቁመዋል።
ፕሬዝዳንት ሙላቱ ሕገ-መንግስታዊ ስርዓትን አስተማማኝ የለውጥ መሳሪያ አድርጎ በመጠቀም ረጅም በማይባል ጊዜ ውስጥ የታሰበውን ግብ ማሳካት እንደሚቻል ያላቸውን ጽኑ እምነት ገልጸዋል። ENA

No comments:

Post a Comment