Wednesday, September 7, 2016

የኢህአዴግ “የተሃድሶ ግምገማ” ሲገመገም!! (ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ)


የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ (ነሐሴ 10-15)፣ እና ምክርቤቱ (ነሐሴ 18-22) ባደረጉት የ15 ዓመት “ተሃድሶ” ጉዞ ግምገማ፣ ሁለት መግለጫዎችን አውጥተዋል - የኢህአዴግ የስራ አስፈፃሚ መግለጫ እና የኢህአዴግ ምክር ቤት መግለጫ። ይህ ጽሁፍም እነዚህን መግለጫዎች መነሻ አድርጎ የተፃፈ ነው። የ“ተሃድሶ ግምገማ” የተባሉት በመሰረታዊ ጥናትና  ምርምር የተደገፉ አይደሉም። (ኢህአዴግ የጥናትና ምርምር አካል የለውም፤ ኢዴፓ እንኳን ገና ሲፈጠር የጥናትና ምርምር አደራጅቷል) ግን ደግሞ ለሃገራችን ትልቅ ትርጉም ያላቸው ነገሮች በመሆናቸው፣ አስተያየቴን መሰንዘር ተገቢ መስሎ ታይቶኛል። 

አገራችን ጠንካራ ፓርቲዎች ያስፈልጓታል። በሰላማዊና በሕጋዊ መንገድ የሚታገሉ ፓርቲዎች (ገዥውም ይሁን ተቃዋሚ ፓርቲዎች)፣ ሕገመንግስቱ ዕውቅና የሰጠውን ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብት መሰረት አድርገው እስከሰሩ ድረስ፣ እንዲጎለብቱ የተቻለኝን ድጋፍ ከማድረግ አልቆጠብም። ለተቃዋሚ ፓርቲዎች በዚህ መልኩ ድጋፌን እለግሳለሁ። ኢህአዴግም ሕገመንግስቱን ብቻ መሰረት አድርጎ ከተጠናከረ፣ ለኔ እሰየው ነው። ለዚህም፣ መልካም ሥራዎች ሲያበስረን እንደማመሰግነው ሁሉ፣ ከሕገመንግስቱ ያፈነገጠ ሲመስለኝና የሕዝቦችን መብቶች ሲያፍን፣ ድምፄን ማሰማት ግዴታዬ ነው። በእርግጥ፣ ‘ኢህአዴግ ሕገመንግስቱን ተግባራዊ ሊያደርግ ይችላል አይችልም’ የሚለው ጥያቄ አከራካሪ ሆኗል። 
በኔ እምነት፣ ኢህአዴግም እንደማናቸውም ፖለቲካዊ ድርጅቶችና ማሕበረሰቦች፣ በዴሞክራሲያዊና ኢ-ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ትግል ውስጥ የሚኖር በመሆኑ፣ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ጥቂት ቢሆኑም እንዲያሸንፉ የበኩሌን አስተዋፅዖ አደርጋለሁ። እንኳን ገዥ ድርጅት ሆኖ፣ የተቃዋሚ ድርጅቶችም ጉዳይ የአገር ጉዳይ ስለሆነ፣ በኔ እምነት ሁሉም ድርጅቶች በተለይ መታደስ የሚያስፈልጋቸው እንዲታደሱ፣ ሁላችንም ኢትዮጵያውያን አስተዋፅኦ ማድረግ ይኖርብናል። 

ግምገማው፣ እስካሁን ድረስ ሕገመንግስቱን ለመተግበር የተከናወኑ ጅምር ሥራዎችን፣ በተለይም በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች የተገኙት እድገቶችን መሰረት ያደርጋል። በጣም የተጋነነ ቢሆንም፣ ማንኛውም ለቀጣይ ለውጥ መሰረት በመሆኑ፣ በውል እንደመነሻ መቀመጡ ትክክል ነው። በእርግማንና በድክመት ብቻ የሚመሰረት ቀጣይ ለውጥ የለምና። አዎንታዊ ጎናቸውን ብቻ ቢያስቀምጥም፣ በሕገመንግስቱ አንቀፅ 41-44 ድረስ ያሉትን ካወጣቸው ፖሊሲዎችና እቅዶች አንፃር የገመገመ ይመስላል - በግልፅ ባይቀመጥም ። 

ሥራ አስፈፃሚውና ምክርቤቱ፣ በህዝቦች ግፊት ራሳቸውን ለማደስ ያነሳሳቸው መሆኑን በመግለጫ መናገራቸውና እውነታውን መቀበላቸው ታላቅ እመርታ ነው። ድርጅቱ የህዝብ ድምፅ በአግባቡ እንዳይሰማና በፍጥነት እንዳይቀረፍ እንዳደረገ አምኗል። በዚህም፣ “የአገራችን ህዝቦች፣ በየአካባቢው የሚታዩ ስህተቶች ይወገዱ ዘንድ፣ ጠንከር ባለ አኳኋን ያካሄዱት ትግል፣ ስራ አስፈፃሚው ለወሰዳቸው የለውጥ አቋሞች ጠንካራ መሰረት ሆነው አገልግለዋል” ማለቱ ይበል የሚያሰኝ ነው። የላይኛው አመራር፣ እንዲህ ኃላፊነት መውሰዱ እንደ አዎንታ መታየት ይኖርበታል:: መግለጫው ሲቀጥል፣ “እነሆ ዛሬ፣ ድርጅታችን በዚህ ችግር ምክንያት የተፈጠረው አደጋ መሰረታዊ መንስኤዎችን፣ በሌላ በማንም ሳያሳብብ፣ በመንግስትና በድርጅት [የ]ሚታይ ቀዳሚ ችግር እንደሆነ ተገንዝቦ… ሥራ አስፈፃሚው በዚህ ረገድ ከራሱ ጀምሮ …” በማለት ኃላፊነትን ወስዷል። ሻዕቢያ፣ ፅንፈኞች፣ ጠባቦች፣ ትምክህተኞች ወ.ዘ.ተ የሚባለው ሰበብ በሁለተኛ ደረጃ መቀመጡም ተገቢ ነው። 
የምራቸውን ከሆነ፣ ከሁሉም በላይ መደነቅ ያለበት የመግለጫው ሃሳብ፣ “የአገራችን ህዝቦች ሰላማዊና ሕጋዊ ትግላቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪያችንን እናቀርባለን” የሚለው ነው። ‘ከእንግዲህ ወዲህ ሰላማዊ ትግሉን አንፈራም፤ አንርበተበትም’፣ ‘ኃይልን ያለ አግባብ አንጠቀምም’ እንደ ማለት ነውና። ይህ ያልተለመደ ነው። ‘የተደራጀ የህዝብ ተሳትፎ አያስፈራንም’ እንደማለት ስለሆነ፣ እሰየው የሚያስብል ንግግር ነው።
ይህ ፅሑፍ፣ ለኪራይ ሰብሳቢነት መገንገንና እየተከስተ ላለው አለመረጋጋት ዋናው ችግር፣ ፀረ-ዴሞክራሲያዊነት እንደሆነና መፍትሔውም ሕገ-መንግሰቱን በተሟላ መንገድ ተግባራዊ ማድረግ ነው ብሎ ሃሳብ ያቀርባል። 

ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ
ከመግለጫዎቹ እንደተረዳሁት፣የዛሬው “የተሃድሶ ግምገማ”፣ የ1993ቱ “ተሃድሶ” አጀማመርን፣ ያኔ የነበረውን መሰረታዊ ኢ-ዴሞክራሲያዊ እና ኢ-ሕገመንግስታዊ አካሄድ ለመገምገም የሞከረ አይመስልም። የ1993 “ተሃድሶ”፣ የፓርቲ ውስጠ ዴሞክራሲ “ከድጡ ወደ ማጡ” የዘቀጠበት፣ ልክ እንደኮሪያው ዲክታተር ፓርክ፣ እንደ ታይዋን ጄኔራል ስሞ፣ ‘ኢኮኖሚያዊ ለውጥ ለማምጣት’ በሚል ሰበብ፣ ሥራ አስፈፃሚው የልጓም የለሽ ግልብያ ዕድል ያገኘበት ታሪካዊ ሂደት እንደነበረ፣ ዛሬ አልገመገመም። 
አንጃዎችን ከነዘርማንዘራቸው ለመምታት በተደረገ ዘመቻ፣ በትግራይ ተወላጆች ዘንድ የደረሰብን መሸማቀቅ፣ በ“ተሃድሶ” ጊዜ የኦህዴድን እና ደህአዴን ድርጅታዊ ነፃነት በሚጥስ ሁኔታ አሸናፊው አንጃና ብአዴን በጥምረት ያደረሱት ቁስል፣ መለስ ብሎ ለማየት ድርጅቱ አልፈቀደም። በ1997 ዓ.ም ደግሞ፣ ተራው ዞሮ ትምክህተኝነትን ለመምታት በሚል ተመቺ ተቀየረ። በዚህም አላበቃም። “አሁን አደጋው ጠባብነት ነው” በሚል ሰበብ በርካቶች ሰለባ ሆኑ። በአጭሩ፣“የኢህአዴግ ዱላ ብሄርን እየለየ ይመታል” ብሎ ማሰብ፣ ኢህአዴግን አለማወቅ ነው። ዱላው ጊዜና ቦታ እየለዋወጠ፣ ሰበብ እያቀያየረ ይነርታል።

ኢህአዴግ፣ በስመ ተሃድሶ የተፈፀሙ በደሎችን መለስ ብሎ ለማየት አልፈቀደም። በአጠቃላይ፣ የድርጅትን ሕግ በጣሰ መንገድ “ሕገመንግስቱ እንጦረጦስ ይግባ” የተባለበት ሂደትን፣ ስለ ዴሞክራሲ ከተፃፈለትና ከተዘመረለት በላይ የዴሞክራሲ ጭላንጭልን ለማጥፋት የወጡት ሕጎችንና ተግባሮችን፣ መብታቸውን ለማስከበር በታገሉ ዜጎች ላይ የደረሰውን ግፍ፣ መለስ ብሎ ለመገምገም የኢህአዴግ አመራሮች አልተዘጋጁም። ማንኛውም ተሃድሶ ወይም ንቅናቄ፣ ከመጀመሪያው የተለያዩ ጉድለቶች ሊኖሩት እንደሚችል እንኳን መገንዘብ አልቻሉም። ከዓመት በፊት ባደረጉት ጉባኤያቸው፣ የህዝብን ድምፅ ለመቀማት (ለምሳሌ በትግራይ ተፈጥሮ የነበረውን ከፍተኛ ተቃውሞ ለማዳፈን)፣ ምንነቱ የማይታወቅ “መልካም አስተዳደር” የሚል ዜማ በማቀንቀን የታችኛውን ሠራተኛ ካጨዱ በኋላ፣ ሂደቱንና ውጤቱን አልገመገሙም። እንዲያውም፣ በጠቅላላ የተረሳ ይመስል “መልካም አስተዳደር” የተባለው ነገር በውል ሳይገልፅ፣ አሁን ደግሞ “ችግራችን ኪራይ ሰብሳቢነት ነው” እያሉ ነው። በነሱ አስተሳሰብ፣ “የአምናው ‘የመልካም አስተዳደር’ ንቅናቄ የት ደረሰ?” የሚል ጥያቄ ከሕዝቦች የሚመጣ አይመስላቸውም። 

የችግሮቻችንን ጥልቀትና መሰረታዊ የመፍትሄ አቅጣጫን በውል ያልተገነዘበ ግምገማ ነው። ችግሮች የተፈጠሩት፣ “ስልጣንን… የግል ኑሮ መሰረት አድርጎ በመመልከትና በአንዳንዶቹም ዘንድ የግል ጥቅም በማስቀደም...” እንደሆነ የሚገልፅ ግምገማ ነው ለኢትዮጵያ ህዝቦች የቀረበላቸው። የመንግስት ስልጣን፣ “... ስልጣን ያለአግባብ ለመጠቀም ለሚሹ ግለሰቦች በመሳሪያነት ማገልገል ሲጀምር…” ነው ችግር የተፈጠረው ይላል - የድርጅቱ ግምገማ። “እንደ እኛ... የሽግግር ኢኮኖሚ ውስጥ ባሉ አገሮች... መንግስትን ከህዝብ አገልጋይነት መስመር እያስወጡ…” ነው ለአደጋ የሚጋልጡት ይላል - ግምገማው። “በምርጫ ካርድ የተሰጠውን ኃላፊነትና አደራ”... የግለሰብ መገልገያ እንዲሆን ሲደረግ ውድቀት ይፈጠራል ይላል።

ኢህአዴጎች፤100% የምርጫ አሸናፊነት ያስከተለውን ጣጣና የነበረውን ጥላሸት ለማየት ያልተቻላቸው አመራር ሆነዋል። “ኪራይ ሰብሳቢነት”ን አንዳንዴ ‘አመለካከት ነው ሲሉ፤... ሌላ ጊዜም፣ ቀለል አድርገው ‘ዝንባሌ ነው’ ሲሉት፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ፣ ‘የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትን በተግባር ያዋሉት አንዳንዶቹ ብቻ ናቸው’ እያሉ... ቀልድ አይሉት ቁም ነገር በህዝቦች ገንዘብና ጊዜ ሲጫወቱ እናያለን። 

“ኪራይ ሰብሳቢነት”፣ በእውነትም ሲታይ ከመሰረታዊ ችግሮቻችን መካከል አንዱ ነው። ነገር ግን፣ ከሱ በባሰና ከሱ ጋር በተያያዘ፣ ሕገመንግስቱ ያጎናፀፈንን (ያወቀልልንን) ሰብዓዊ መብት ክፉኛ መረገጡ ነው - ትልቁ መሰረታዊ ችግር። ሕብረተሰቡ፣ ‘መብታችን ይከበር’ ሲል፣ የድርጅቱ አመራሮች፣ ‘የአመለካከት ችግርን እኛ ገምግመን ቀርፈናል፤ አንዳንዶቹ ሙሰኞች ላይ ደግሞ እርምጃ እንወስዳለን’ ብለው ያሾፋሉ። ምን አይነት እርምጃ? በማን ላይ? የሚለው ጥያቄ ገና የሚታይ ነው። ከወዲሁ ሲታይ ግን፣ ትርጉም የለውም። ቱባ ቱባዎቹንና ቢሊዮን ብር የሚያንቀሳቅሱትን በመተው፣ እታች የሚርመሰመሱትንና አለኝታ የሌላቸውን መኮርኮም ምን የሚሉት ስራ ነው? “አንፀባራቂ እርምጃ”? ሕገመንግስቱን በግላጭ የሚጥሱ ትላልቅ ዝሆኖችን ትተው፤ ጀማሪና ‘ጋሻ-የለሽ’ የሆኑትን፣ ጀማሪ ስራ አስፈፃሚ፣ ጀማሪ ሚኒስትር፣ ጀማሪ ኮሚሽነር፣ ጀማሪ ጄኔራል እና ግንኙነት አለው ያሉትን ጨማምረው... “እርምጃ ወስደናል” በማለት፣ ተቃውሞን ለማስታገስና ጊዜ ለመግዛት ይሞክሩ ይሆናል። 
ነገር ግን፣ እውነተኛ እድሳት፣ ኔትወርኩ ባልተበጠሰበት ሁኔታ፣ ተጠያቂነት፣ ግልጽነት፣ የሕግ-የበላይነት በሌለበት መንገድ ሊፈፀም በእጅጉ አስቸጋሪ ነው፡፡ ራሳቸውን ለመቀየርና ሃገሪቱን አሁን ካለው ቀውስ ለማዳን ከፈለጉ፣ “ሕገመንግስቱን ሸርሽረን ዴሞክራሲያዊ ምህዳሩን እያፈነው ነው። ይህም በውስጠ-ፓርቲ ፀረ-ዴሞክራቲክ አመለካከትና አሰራር መዘፈቃችን፤... መንግስታችን ሕገመንግስቱን የሚጥስ ድርጊት እንዲፈፅም ማድረጋችንና የህዝቦችን መብት ማፈናችን ስህተት ነበር” ብለው ለእውነተኛ እድሳት ራሳቸውን ዝግጁ ማድረግ በተገባቸው ነበር። 
ውሃ ቢወቅጡት እንቦጭ
ለመሆኑ ኪራይ ሰብሳቢነት ምንድን ነው? ኪራይ ሰብሳቢነት እንዴት ሊጋነን ይችላል? እንዴት በቀጣይነት ተፅእኖውን እናሳንሰው የሚለውን በአጭሩ ማየት ተገቢ ነው። ኪራይ ሰብሳቢነት ቱሎክ እና ክሩገር የሚባሉ ኢኮኖሚስቶችን መሰረት ያደረገ ፅንሰ ሓሳብ ነው። በነፃ ገበያ ስርዓት ገበያው ያለአስፈላጊ ጣልቃገብነትና ምንም ዋጋ ሳይጨምሩ ነፃ ገበያውን የሚያተራምስና ከሰሩበት በላይ ትርፍ ማካበትን እና ተጠቃሚነትን በማረጋገጥ ልማትን የሚያደናቅፍ ሂደት ነው። ኪራይ ሰብሳቢነት በሽግግር ላይ ባሉ አገሮች የሚብስ ቢሆንም ባደጉ አገሮች ጭምር ትልቅ ህብረተሰባዊ በሽታ ነው። ፖለቲካዊ ስርዓቱ ሲበሰብስ (decadence) ባደጉ አገሮችም ቢሆን ኪራይ ሰብሳቢነት በከፍተኛ ደረጃ እንደሚከሰት የዓለም ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት እና ዋናው ኢኮኖሚስት የነበረው ፕሮፌሰር ስቲጊለትዝ ስለ አሜሪካና በሌላው ዓለም ስላለው ኪራይ ሰብሳቢነት፣ ከፖለቲካው ጋር አያይዞ እንዲህ ይገልፀዋል፡-

“Three themes resonate around the world; that markets were not working the way they were supposed to for they were obviously neither efficent nor stable, that the political system had not corrected the market failures and that the economic and political systems are fundamentally unfair. The three themes are intimately interlinked: The inequality is cause and consequence of the failure of the political system, and it contributes to the instability of our economic system, which inturn contributes to increased inequllaity - a vicious downward spiral into which we have descended, and from which we can emerge only through concerted policies”.
በተጨማሪም ስቲግሊዝ እንዲህ ይላሉ፡ “especially in the United States, it seems that the political system is more akin to ‘ one dollar one vote’ than to ‘one person one vote’” ቀደም ብለው Vanity fair በሚባል መፅሄት በፃፉት ጽሁፍ፣ “Of The People, For The People, By The People” የተሰኘው አባባል፣ እንዴት “Of The 1%, For The 1%, By The 1%” ተብሎ እንደተተካ በመግለፅ የአሜሪካኖችን ቅሬታ ያስታውሳሉ። በአሜሪካ ውስጥ “Occupy Wallstreet” በሚል ስያሜ ሲካሄድ የነበረውን እንቅስቃሴ፣ በጊዜው ከነበረው የቱኒዚያና የግብፅ ህዝባዊ አመፅ ጋር ያመሳስሉታል - ስቲግሊዝ። እኛስ ቢሆን፣ በኦሮሚያ ክልል እና በአማራ ክልል የተከሰተው ተቃውሞ ከዚህ ጋር ሊያያዝ አይችልም እንዴ? ይህ ማለት፣ ሕዝብ... በብሄር የተቃኘ ጥያቄ ሳይሆን፣ በአጠቃላይ ከፖለቲካዊና ከኢኮኖሚያዊ መዋቅሩ ጋር የተያያዘ የፍትሕ፣ የእኩል ተጠቃሚነት፣ የዴሞክራሲያዊ ተሳትፎና የተመጣጣኝ ሚና ጥያቄዎችን እያነሳ እንደሆነ መረዳት ስንችል ነው የኛ ሃገር ጉዳይም ከሌሎች ሃገሮች ፖለቲካዊ ትኩሳት በመሰረቱ የተለየ ሊሆን አይችልም ብለን መሞገት የምንችለው። 

ይህ የስቲግሊቲይዝ አባባል ከትችት አላለፈም፤ ኪራይ ሰብሳቢነት ፖለቲካዊ መነሻው ፖለቲካዊ ነው ማለታቸው ትክክል ሆኖ፣ ተራ ፖለቲካ አድርገው ማየታቸው ግን ስህተት ነው ይላል ፒተር- “Stiglitz and A Theory of rent Seeking Society” በሚለው ጽሁፍ። In a fundamental sense, the problem is that Stiglitz is thinking in terms of ordinary politics when he must make the move that Buchanan and Tullock made, and look at fundamental changes to the rules of the game. (The Constitutional Level of Analysis)

በኢትዮጵያ ውስጥ ስልጣን የግል መጠቀሚያ የማድረግ አመለካከትን መታገል ተገቢ ነው። በሙስና የተዘፈቁት ላይ እርምጃ መውሰድ የማይታለፍ ነገር ነው። መፍትሄው ግን እጅግ ከዛ በላይ ነው፤ ህዝቦች ሕገመንግስታዊ መብቶቻቸው ሲረጋገጥ፣ ዴሞክራሲያዊ ምህዳሩ እየሰፋ ሲሄድ ኪራይ ሰብሳቢነትን መዋጋት ብቻ ሳይሆን ህዝቦች ለልማት በተሞላ መንገድ ተነቃንቀው አገሪቱ በቀጣይነትና በተሟላ መልኩ የምታድግበት ሁኔታ መፍጠር ይችላሉ የሚባለው። ስልጣን ተቆጣጣሪ ስርዓት ካልተዘረጋለት ሊያባልግ እንደሚችል ጥንት ታልሞ የተፈታ ነገር ነው፤ ለዚህም ነው የፖለቲካ ሳይንስ ባላሞያዎች የክትትል እና የቁጥጥር ስርዓት ማበጀት ቁልፍ መፍትሔ ነው ብለው የሚከራከሩት። 
ዴሞክራሲ እና ኢህአዴግ ለየቅል ናቸው እንዴ?

ሥራ አስፈፃሚው ይሁን ምክርቤቱ፤ የአገራችንን ሕገመንግስታዊ ትግበራ ዴሞክራሲያዊ ግንባታ የገመገመ አይመስለኝም። በምክርቤቱ መግለጫ፤ “ዴሞክራሲያችን ስፋትና ጥልቀት እያገኘ ተጉዟል። የአዲሲቱ ኢትዮጵያ የፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደትም በተቀመጠለት አቅጣጫ ቀጥሏል” ይላል። ህዝቡ ግን ምን እየሆነ እንዳለ በደምብ ይገነዘባል፤ የሚኖረውን ኑሮ በቅጡ ያውቀዋል፣ ሊጠፋበትም አይችልም። ሌላው ቢቀር እንዴት ለይስሙላ እንኳን በተለይ የኦሮሞ ፕሮቴስትና የአማራ ተቃውሞ ሰልፍን አስመልክቶ በዴሞክራሲ ምህዳሩ ላይ እነዚህ ጉድለቶች አሉ ብለው መጥቀስ ያቅታቸዋል። 
ከ200 ዓመታት በላይ የዴሞክራሲያዊ ግንባታ እያካሄደ ያሉት የምዕራብ አገሮች የዴሞክራሲ እጥረት በተለያዩ ጊዜያት የሚገለፅበት እና ድክመቶች ለማረም ጥረት በሚደረግበት ሁኔታ ይህ ወደ ዴሞክራሲ ሽግግር ላይ ያለ አገር፤ ያውም ሊብራል ዴሞክራሲን የሚያብጠለጥል ድርጅት እንዴት ከዴሞክራሲ ግንባታ ጋር በተያያዘ ያሉ ተግዳሮቶችን አይገመግምም? ኢህአዴግ ዴሞክራሲያዊ ነው ብንል እንዃ ህብረተሰባዊ እንቅስቃሴ ስለሆነ ኢ-ዴሞክራሲያዊ ሃይሎች ብቅ ጥልቅ ማለታቸው ስለማይቀር፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ ወዋቅሩ ገና ያልዳበረ በመሆኑ ዴሞክራሲያዊ ምህዳሩ ደረጃ በደረጃ እየሰፋ ቢሄድ እንኳ “ሁለት እርምጃ ወደ ፊት አንድ እርምጃ ወደ ኋላ” ነው የሚሄደው። 

ዴሞክራሲያዊ ምህዳሩ “አንድ እርምጃ ወደ ፊት፣ አምስት እርምጃ ወደ ኋላ” በሆነበት ሁኔታ፣ ህዝቦች መብታቸውን ለማረጋገጥ በያዘው ከፍተኛ እንቅፋት በሚገጥምበት ሁኔታ ፖለቲካ ተቃዋሚዎች በዴሞክራሲ ግንባታ ያላቸውን አዎንታዊ ተራ የማይገነዘብ ድርጅቶችን ለማዳከም መንግስታዊ ፖሊሲ እንደሆነ በሚያስመስል ሁኔታ ታትሮ የሚሰራ፣ የጋዜጠኞችና የተቃዋሚ አባሎች መታሰር ኖርማል የሆነበት ሁኔታ ወዘተ ስለዴሞክራሲያዊ ምህዳሩ አለመገምገም ምን ይባላል? ጭራሽ “ዴሞክራሲያችን ስፋትና ጥልቀት እያገኘ ተጉዟል” ብሎ ግትር! ምክር ቤቱ፤ “ይህ ስራ በድርጅታችን ውስጥ በሚካሄድ ትግል ብቻ ሊስተካከል እንደማይችል ሁሉ ህዝቡ በተናጠል ብቻውን የሚያካሄደው ትግልም የሚፈለገውን ለውጥ ሊያስመዘግብ እንደማይችል ይገነዘባል” ይላሉ:: ህዝቡ ውስጥ የተለያዩ ሃሳቦች የሚያንፀባርቁ ፖለቲካዊ ድርጅቶች ማህበራዊ ስብስቦች፣ የተለያዩ ግለሰባዊና ቡድናዊ ፍላጎቶች ወ.ዘ.ተ እንደሌሉ እና “በተሃድሶ” ምንም ሚና እንደማይኖራቸው ታሳቢ በማድረግ:: የተለያዩ መደቦችና ሕብረተሰባዊ ክፍሎች የየራሳቸው ፍላጎትና ሰልፍ ሊኖራቸው እንደሚችልም እሳቤው ውስጥ የለም፡፡ ላባደሩ፣ ገበሬው፣ ከበርቴውና ንኡስ ከበርቴውን እንደ አንድ የሚያይ ጥቅል ድምዳሜ ነው በመግለጫው የተስተጋባው። የሕብረተሰቡን የተለያዩ አመለካከቶች የሚያንጸባሩቁና ተደራጅተው ህዝቦችን የሚያታግሉ ተቃዋሚ ድርጅቶች ና ነፃ ማህበራት ሳያካትት አገሪቱን አድሳሎህ ብሎ ይፎክራል። 
ርእየተ ዓለማዊ (Ideological) እና ፖለቲካዊ ክስረት
አብዮታዊ ዴሞክራሲ አይዲዮሎጂ፤ በ“ተሃድሶው” አካባቢ አቶ መለስ ከፃፉት በኋላ መደርደርያ ውስጥ የተቀመጠ ነው የሚመስለው። ስለ ዴሞክራሲ እየተፃፈ ቀለሙ ሳይደርቅ ፀረ-ዴሞክራቲክ አስተሳሰብና ድርጊት ጎልቶ የሚታይበት ክስተት ነበር ማለት ይቻላል። እንደ ኢህአዴግ ስለ ዴሞክራሲ የሚዘምር ያለ አይመስለኝም። ሆኖም ዴሞክራሲ ተብሎ ተነግሮ፣ የንግግሩ ገድል ማሚቶ ሳይርቅ፣ ዴሞክራሲውን መቃብር የሚያስገባ ስራ ይሰራል። 
ርእየተ ዓለማዊና ፖለቲካዊ ክስረቱን ለማየት ከዚህ በታች የዘረዘርኳቸውን ነገሮች ማየት በቂ ይመስለኛል፡-
“የምንገነባው ስርዓት ሕብረብሔራዊ ነው”ይልና ዞር ብሎ ደግሞ
ያለ ኢህአዴግ መንገድ ሌላው ሁሉ የጥፋት መንገድ ነው
ሰራዊታችን የአብዮታዊ ዴሞክራሲየመጨረሻ ምሽግ ነው 
በአሁኑ ጊዜ አብዮታዊ ዴሞክራሲን የሚወክለው ኢህአዴግ ነው። 
ሰራዊቱ፤ ኢህአዴግን ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ አፈንግጦአል ብሎ ካመነ፣ኢህአዴግ ላይም እርምጃ መውሰድ እንደሚችል ሁሉ፣
አብዮታዊ ዴሞክራሲ, ዴሞክራሲን ሊደርስበት የሚችለው ጫፍ የማድረስ ዓላማ አለው። ከሊበራል ዴሞክራሲ የላቀ ዴሞክራሲያዊ ነው። 
ኢህአዴግን የሚተካው ሊብራል የሃብታሞች ድርጅት ነው
መንግስት (state) መስተዳድር (government) ፓርቲ ለያይቶ የማያይ
በህዝቦች ውስጥ ያለውን ሁኔታ ማንበብ የማይችል ግዑዝ ድርጅት
ወገኑንና ጠላቱን መለየት ያቃተው ድርጅት
የመንግስት ስልጣንን እንደማትግያ ተጠቅሞ፣ በስፋት የሚመለምል ድርጅት
ውስጣዊ ፖለቲካዊ ህይወቱ የሞተ፣ አድር-ባይነትና አድር-ባዮች የነገሱበት ድርጅት
እውነተኛ ወጣት ምሁራን የማይጠጉት ድርጅት
ድሉን አሳልፎ እየሰጠ ያለ ፓርቲ

ኢህአዴግ ዓለም አሉኝ ከሚላቸው ሕገመንግስታት ውስጥ የተሻለውን ሕገመንግስት አቀንቃኝ በመሆን ለሶስቱም የሰብዓዊ መብት ትውልዶች (three generations of human rights) እውቅና የሰጠ እና በነበረው ነባራዊ ሁኔታ ህዝቦች በተለያየ ደረጃ ተወያይተው ያፀደቁት (ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ በመጋቢት 11/2016 እ.አ.አ. ከአዲስ ስታንዳርድ መፅሄት ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ፤ በህገ-መንግስቱ ዙርያ በተደረገው ውይይት በእያንዳንዱ ቀበሌ በአማካይ ከ 100-150 ሰው ይሳተፍ እንደነበር ገልፀዋል፤ ይህ ማለት ሕገመንግስቱ በከፍተኛ የህዝብ ተሳትፎ እንደፀደቀ አመላካች ነው። በዚህ ጉዳይ ላይ ከእርሳቸው በላይ እማኝ የሚሆን ሰው ያለ አይመስለኝም) ( legitimacy ብዙ ጥያቄ የሚነሳ ቢሆንም) ፤ በዚህ መሰረት ተግባራዊ ማድረግ ሲጀመር በአገራችን ሰላም፤ መረጋጋትና እድገት ማቆጥቆጥ ቢጀምርም የኋላ ኋላ ግን ድርጅቱ መስመሩን አሽቀንጥሮ ስለጣለው. እነሆ ሰላምና መረጋጋቱ ችግር ውስጥ እንዲዘፈቅ አድርጎታል፤ በአይናችንም እያየነው ነው። የኢትዮጵያ ህዝቦች ሕገመንግስቱን መተግበር ሲጀምሩ ለኢህአዴግ የሰላምና የይሁኔታ ባንዲራ (ሰንደቅ አላማ ማለቴ አይደለም) ቢሰጡም፣ ከጊዜ በኋላ ድርጅቱ የተሰጠውን ሃላፊነት ወደ ታች እየደፋ የሄደበት እና ህብረተሰቡም በፓርቲው ውዥንብር የገባበት ሁኔታ እናያለን። ከዚህ ሕገመንግስት በተሳሰረ ፕሮፌሰር እስቄል ገቤሳ የኦሮሞ እንቅስቃሴ በሚመለከት እንዲህ ብለው ነበር፤ 

“Finally the central demand of the Oromo national movement as articulated in the political program of Oromo Liberation Front (OLF) was achieved when the right to self determination becomes part of the 1995 Ethiopian constitution. For Oromo nationalists therefore, the FDRE constitution, with all its shortcomings, can and should be deployed as an instrument that confers legality on the historic and yet unfulfilled demand of the Oromo and others. Not to use it would amount to disavowing one’s own history.”
ዶክተር ፀገዬ አራርሳ፤ ሕገመንግስቱ ለሁሉም ዓይነት ግንኙነት መነሻ መሆን እንዳለበት እንደሚስማሙ ይገለፃሉ። ሕገመንግስቱን መሰረት በማድረግ፣ በሰላማዊ መንገድ ወደ ዴሞክራሲ ሽግግር ማድረግ የሚቻል መሆኑን ደግሞ ፕ/ር ህዝቅያስ በሚከተለው ሁኔታ ይገልፃሉ፡-
“At no other time in Ethiopia’s political history has a non violent transition to democracy more desirable and achievable. Additionally, at no other time in the past have Ethiopians viewed the Oromo as a force for democratizating the Ethiopian empire state.”

አሁን ባለው ሁኔታ መላው የኢትዮጵያ ህዝቦች በተለያዩ መንገዶች እና አገላለፆች ሕገመንግስቱ ይከበር እያሉ ነው። አገር ውስጥ ያሉ ተቃዋሚዎችም ቢሆኑ በአንዳንድ የሕገመንግስቱ አንቀፆች ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ እና ተአቅቦ ቢኖራቸውም፣ በድምሩ ሲታይ ግን ሕገመንግስቱ ይከበር በማለት እየተንቀሳቀሱ ናቸው። ከፅንፈኞች እና ከኢህአዴግ ውጭ ያሉት ሃይሎች በሙሉ ሕገመንግስቱ ይከበር እያሉ ነው። ሕገመንግስቱ ይከበር የሚለውን መንፈስ አሰባሳቢ መፈክር እየሆነ መጥቷል። አንጋፋው ፖለቲከኛ አቶ ሌንጮ ለታ ለኢሳት ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንዲህ ብለው ነበር። አቶ ሌንጮ ለምን የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) በደርግ ጊዜ የመገንጠል ፕሮግራም ማራመድ እንዳስፈለጋቸው ሲገልፁ በወቅቱ በነበረው ዓለማዊ የደርግ መንግስት የአስተዳደር ነባራዊ ሁኔታ ምክንያት መሆኑንና ትክክል እንደነበር፤ አሁን ግን ከሁኔታዎች መቀየር ጋር ተያይዞ እንዲሁም የኢፌድሪ ሕገመንግስት ብሄሮች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደርና እስከ መገንጠል መብት ያረጋገጠ በመሆኑ የፌደራል ስርዓቱ ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን በሰላማዊ መንገድ መታገል አለብን በማለት ያብራራሉ። በመቀጠልም የኦሮሞ ፕሮቴስት ዋና ጥያቄ፣ መብቶቻችን ይከበሩ የሚል ስለሆነ መንግስት በአንጻሩ የወሰደው እርምጃ ይኮንናሉ። ከመንግስት ባለስልጣኖች ለመወያየት አገር ውስጥ ቢገቡም የሚያገኛቸው አጥተው ወዳሉበት ተመልሰዋል። እኚህ አንጋፋ ፖለቲከኛ ሕገመንግስቱን ተቀብለው፤ የትጥቅ ትግል በማካሄድና መንግስትን በሃይል በማውረድ ዴሞክራሲ መገንባት አይቻልም በማለት በሰላማዊ መንገድ ብቻ መታገል አለብኝ ብለው አምነው ሃገር ቤት በመጡበት ጊዜ በመንግስት ዘንድ ተቀባይነት አለማግኘታቸው እጅግ የሚያሳዝን ነው። በብቃታቸውና በተቀባይነታቸው ብቻ ፈሯቸው እንዴ? 

”ተሃድሶው” በማህበረ-ኢኮኖሚያዊ እድገት ዙርያ የነበረው ግምገማ በድል የታጀበ ቢሆንም የሕገመንግስቱ አንቀፅ 9 (የሕገመንግስት የበላይነት) እንዲሁም በሕገመንግስቱ የተካተቱት ሌሎች መሰረታዊ መብቶችና ነፃነቶች (ከአንቀፅ 10-40) ያሉትን ሳይነካ እንደ ዘበት የተዘለለበት ሁኔታን አይተናል። እነዚህ ደግሞ የህዝቦች መሰረታዊ መብቶች ናቸው። ለምን? ኢህአዴግ አይጠቅምም ስላለ? ጉዱ እንዳይወጣበት? ነባራዊውን የፖለቲካ ኢኮኖሚ ሁኔታ ማንበብ ስላልቻለ? የሆነ ሆኖ በማናቸውንም መለኪያ ኢህአዴግ ድሉን አሳልፎ የሰጠ ድርጅት ሆኗል ማለት እንችላለን።
የትምክህትና ጠባብነት አባዜ
ኢህአዴግ ርእዮተ-ዓለማዊና እና ፖለቲካዊ ክስረት ያጋጠመው ድርጅት ስለሆነ እንደ አንድ ለማየት ያስቸግራል:: በመሆኑም ትምክህትና ጠባብነት በህወሐት፣ በኦህዴድ፣ በብአዴን እንዲሁም በደህአዴግ የተለያዩ ትርጉም ይሰጣቸው ይሆናል። አሁን ባለው ሁኔታ ፖለቲካዊ ስርዓቱ ካለው ችግር አንፃር ከማየት ይልቅ አንዱ ድርጅት ሌላውን የሚወቅስበት እና ችግሮቻቸውን ውደ ሌላው የሚያጣብቁበት ( blame shift ) የትግል ዘዴዎች እንዳይሆኑ ማየት ተገቢ ነው። ትምክህትና ጠባብነት የተወሰኑ ልሂቃን ለራሳቸው ግላዊ ጥቅም ሲሉ በተሟላ መንገድ የሚጠቀሙበት አመለካከት ነው። 

በህዝቦቻችን ውስጥ ያለውን ኃላቀርነት እና የዲሞክራሲ ባህልና ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት አለመጎልበት ተጠቅመው፣ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ የሌላቸው መሪዎች ወይም የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰባቸውና ተግባራቸው ለመሸፈን ሲሉ የሚጠቀሙበት ዘዴ ነው። የፀረ-ዴሞክራሲያንና እና የሙሰኞች ምሽግ ነው። 

ዋናው ጉዳይ እነዚህ አመለካከቶች መቼ ነው በከፍተኛ ደረጃ አደገኛ የሚሆኑት የሚለውን ማየት አስፈላጊ ይመስለኛል። እነዚህ አስተሳሰቦች በህብረተሰቡ ውስጥተ ደብቀው ለዘመናት ሊኖሩ ቢችሉም አደገኛ የሚሆኑት ግን የዴሞክራሲ አስተዳደሩ ላይ ከፍተኛ ችግር ሲኖር ነው በማለት ወጣቱ የፖለቲካል ሳይንስ ምሁሩ ናሁሰናይ በላይ በሚከተለው መልክ ያብራራሉ። እንደ እሳቸው እሳቤ፤ በዲሞክራሲ እጦትና የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳስብና ተግባር መካከል ያለው መስተጋበር ልክ “እንደ ዝንብና ቆሻሻ አድርገህ ማየት ይቻላል” ይላሉ፤ በመቀጠልም ቆሻሻ (የዴሞክራሲ እጥረቱ) በሌለበት አካባቢ አንድ ሁለት ዝንቦች (የኪራይ ሰብሳቢነት፣ ትምክህትና ጠባብነት አስተሳሰብና ተግባር) ሊኖሩ ይችላሉ፤ ድምጽ ካልሰማህ መኖራቸው አታውቅም። ከዝንብ ነፃ የሆነ አካባቢ ያለህ ይመስልሃል። ከፍተኛ ቆሻሻ በሚከማችበት ሁኔታ የዝንብ መአት አያስቀምጥህም” በማለት የሁለቱን ምክንያታዊ ጥምረት ያብራራሉ። በዴሞክራሲያዊ አስተዳደር ረገድ ችግር በሚኖርበት ጊዜ እነዚህ ለግል ጥቅማቸው የሚሯሯጡ ልሂቃን፤ ያለ ምንም ከልካይ ወይም ሃይባይ ወለል ያለ ሜዳ ስለሚያገኙ እንደፈለጉ ይጋልቡታል ማለት ነው። በዚህ ጊዜ ሁኔታዎች ሁሉ አደገኛ ይሆናሉ። መፍትሄውም ዝንቦች (የኪራይ ሰብሳቢነት፣ ትምክህትና ጠባብነት) ከማስወገድ በላይ ቆሻሻውን ማስወገድ ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ማለት ነው። ፀረ-ዴሞክራቲክ አስተዳደር የሚባል ቆሻሻ!!
ግምገማዬን ሳምንት እመለስበታለሁ፡፡ ለዛሬ ግን ወጣቱ ናሁሰናይ የላከልኝን ከፊታውራሪ ተክለሃዋርያት ተክለማርያም የህይወት ታሪክ የተቀነጨበ አስተማሪ ጥቅስ (በተለይ ለባለስልጣኖቻችን) ላካፍላችሁ፡- 

“ንጉሶች እና ባለጊዜዎች ከጥፋት የሚደርሱት በከንቱ ውዳሴና በከንቱ ትምክህት ነው። ፍጡሮች መሆናቸውን ይረሱትና ሁሉንም ማድረግ የሚችሉ፣ ሁሉም ለነሱ ደስታና ክብር የተፈጠረ ይመስላቸዋል። በዙሪያቸው የሚከቧቸው ጥቅም ፈላጊዎች ሁሉ ይህንን እያስመሰሉ እንዲያምኑበት ያደርጓቸዋል። ታዲያ ከሕግ በላይ መሆን፤ ከፍጡር በላይ መሆን ያምራቸውና በዘፈቀደ እንስራ ይላሉ። የሚከራከሯቸውን የሚያደንቋቸውን እንደ ጠላት ያዩዋቸዋል ያጠቋቸዋልም።” (ይቀጥላል) Read more here

No comments:

Post a Comment