Tuesday, December 8, 2015

የኢትዮ-ጅቡቲን የሃዲድ መስመር የሚገነባው ኩባንያ በስርቆት 20ሚ. ብር አጣሁ አለ

- 1500 ጥበቃዎች ተመድበዋል
- ለጥበቃ በወር 3ሚ. ብር ያወጣል

   የኢትዮ - ጅቡቲ የሃዲድ መስመርን የሚዘረጋው ቻይና ኩባንያ ከስርቆት ጋር በተያያዘ 20 ሚሊዮን ብር ገደማ ኪሳራ እንደደረሰበት የታወቀ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት ስርቆቱን ለመከላከል ከ1500 በላይ ጥበቃዎች  በሀዲድ መስመሩ ላይ ተመድበዋል፡፡ 
የቻይናው ኩባንያ CREC እንደገለፀው እስካሁን ሲሚንቶን ጨምሮ የተለያዩ የግንባታ ቁሳቁሶች እንዲሁም የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ሽቦዎች በሌቦች ተሰርቀውበታል፡፡ 
ስርቆቱ የ20 ሚ. ብር ኪሳራ በተጨማሪ ፕሮጀክቱ በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዳይጠናቀቅ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳደሩን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ኩባንያው ተመሳሳይ ስርቆቶችን ለመከላከል ከ“አጋር” የጥበቃ ድርጅት ጋር ውል በመግባት፣ ከ1500 በላይ ጥበቃዎችን ቀጥሮ በሀዲዱ መስመር ላይ ለማሰማራት የተገደደ ሲሆን ለዚህም በየወሩ 3ሚ. ብር እንደሚያወጣ አስታውቋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም 160 ያህል የፌደራል ፖሊሶችም የባቡር ፕሮጀክቱ ሌት ተቀን ይጠብቃሉ ተብሏል፡፡
በቅርቡ የእርዳታ እህል በማጓጓዝ የሙከራ ስራ የጀመረው የኢትዮ-ጅቡቲ ባቡር ፕሮጀክት፤ መቼ ወደ ሙሉ አገልግሎት እንደሚገባ የተጠየቁት የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደረጀ፤ ከሲግናሊንግና መሰል ጉዳዮች ጋር የተያያዙ ያላለቁ ስራዎች በመኖራቸው በትክክል መቼ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ለማወቅ አይቻልም ብለዋል፡፡ 
በአሁን ሰአት የክብደት ሙከራ እየተካሄደ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ደረጀ፤ የእህል ማጓጓዝ ስራውም የሙከራው አካል ነው ብለዋል፡፡ 
በቅርቡ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎቱንና ፕሮጀክቱን የሚያስተዳድር ኩባንያ በጅቡቲና በኢትዮጵያ የጋራ ስምምነት እንደሚመሠረት የጠቆሙት ኃላፊው፤ ፕሮጀክቱን ሁለቱ ሃገራት በጋራ እንደሚያስተዳድሩት ገልፀዋል፡፡ 
በባቡር ፕሮጀክት መስመሩ ላይ እየተፈፀመ ነው ስለተባለው ስርቆት የተጠየቁት ሃላፊው፤ ይህ የሚመለከተው የግንባታ ስራውን ኮንትራት ወስዶ የሚያከናውነውን ኩባንያ እንደሆነ ጠቁመው፤ “ጥበቃ መቀጠሩ በፊትም የነበረ ነው፤ እንኳን አዲሱ ፕሮጀክት የድሮው የኢትዮ ጅቡቲ ሃዲድም ይጠበቃል” ብለዋል፡፡ 
አንዳንድ ጥቃቅን ስርቆቶች ማጋጠማቸውም የተለመደ ነው፤ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ላይም ይከሰት ነበር ያሉት አቶ ደረጀ፤ ከጥቃቅን ስርቆት ውጭ ግን የተደራጀ ሌብነት ሊኖር አይችልም ብለዋል፡፡ ፕሮጀክቱን ማህበረሰቡ ራሱ እንደሚጠብቀው፣ የመንግስት የፀጥታ ሃይሎችም ጥበቃ እያደረጉለት መሆኑንም ተናግረዋል፤ ኃላፊው፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን የቻይናው ኩባንያ በስርቆት የ20ሚ. ብር ኪሳራ ደርሶብኛል ብሏል፡፡   

Source: Addis Admas

No comments:

Post a Comment