Monday, November 28, 2016

መንግሥት ሕዝቡ ላቀረበው ጥያቄ ምላሽ ሳይሰጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዳይነሳ ኢዴፓ አሳሰበ

 ኢዴፓ አንድ ጠንካራ ፓርቲ ለመፍጠር ማንኛውንም ዕርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ ነኝ አለ
በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የተፈጠረውን ቀውስ ባለው የሕግ አግባብ መፍታት እንደማይቻል አምኖ መንግሥት ከመስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁ፣ ተገቢና የሚስማማበት ዕርምጃ መሆኑን የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ገለጸ፡፡ ነገር ግን በአገሪቱ ዘላቂ መፍትሔ የሚመጣው፣ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ፣ በወታደራዊ ጣልቃ ገብነት፣ በጥልቅ መታደስና ካቢኔ በመቀየር ሳይሆን ሕዝቡ ላቀረባቸው ጥያቄዎች ተገቢ ምላሽ በመስጠት በመሆኑ፣ ይኼንን ተግባራዊ ሳያደርግ አዋጁ እንዳይነሳ ኢዴፓ አሳስቧል፡፡
የኢዴፓ መሥራችና ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ልደቱ አያሌው ኅዳር 15 ቀን 2009 ዓ.ም. በቅሎ ቤት በሚገኘው የፓርቲው ጽሕፈት ቤት ከፓርቲው አመራሮች በጋራ በመሆን በሰጡት መግለጫ እንዳስረዱት፣ መንግሥት ሕዝቡ ያቀረበውን የዴሞክራሲ፣ የሰብዓዊና ኢኮኖሚያዊ፣ በእኩልነት የመልማትና ፍትሕ የማግኘት ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት እንዳለበት መንግሥት በተደጋጋሚ መናገሩን፣ የአገሪቱ ርዕሰ ብሔርም በ2009 ዓ.ም. የፓርላማ መክፈቻ ንግግር ባደረጉበት ወቅት ማረጋገጣቸውን አስታውሰዋል፡፡ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ለመደራደር፣ ሕዝቡን በስፋት ለማወያየትና ፖሊሲዎችንም እስከማሻሻል የሚደርሱ ዴሞክራሲያዊ እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ ጭምር ቃል የተገባ ቢሆንም፣ እስካሁን ምንም አለመደረጉን አቶ ልደቱ አስረድተዋል፡፡ በመሆኑም በተለይ ሕዝቡ ያነሳቸውን የመብት ጥያቄዎች ምላሽ ሳያገኙ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ቢነሳ፣ አገሪቱን ሊገታ ወደማይችል ችግር ውስጥ ሊያስገባ እንደሚችል ሥጋታቸውን ተናግረዋል፡፡
የሕዝቡ ፍላጎት ኢሕአዴግ ታድሶና ካቢኔውን እንደገና አዋቅሮ አቅሙን በማጠናከር እንዲመራው ሳይሆን፣ ላቀረባቸው ጥያቄዎች በዓይን የሚታይ ተግባራዊ ዕርምጃ በመውሰድ ለውጥ እንዲያመጣለት መሆኑንም አክለዋል፡፡ ኢሕአዴግ አሁን የያዘውን የመታደስና ካቢኔውን የማስተካከል ለውጥም ጎን ለጎን ማስኬድ እንደሚችልም ጠቁመዋል፡፡
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ያስገኘውን ጊዜያዊ መረጋጋት ተጠቅሞ ወደ ትክክለኛ የፖለቲካ መፍትሔ መግባት የመጨረሻው አማራጭ መሆኑን የተናገሩት አቶ ልደቱ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ለዳያስፖራውና በዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ እንዳስረዱት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በቅርቡ የሚነሳ ከሆነ፣ አገሪቱን ሌሎች የጎረቤት አገሮች ወደገቡበት ቀውስ ሊያስገባ ስለሚችል ትኩረት ሰጥቶ ማሰብ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ኢዴፓ ሰባተኛ ጠቅላላ ጉባዔውን ማካሄድ የነበረበት መስከረም 26 ቀን 2009 ዓ.ም. ቢሆንም፣ አባላቱን ለመጥራትም ሆነ ጋዜጣዊ መግለጫ ለመስጠት ባለመቻሉ፣ በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ለስድስት ወራት እንዲራዘም ማድረጉን ገልጿል፡፡
የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴና የጉባዔው አዘጋጅ ኮሚቴ አባል አቶ ግዛቸው አንማው እንዳስረዱት፣ ጠቅላላ ጉባዔውን ማራዘም የተፈለገው ፓርቲውን ወደ አንድ የላቀ የጥንካሬ ደረጃ ለማሸጋገር ነው፡፡
የጉዳዩ ዋና ባለቤት የሆነው ሕዝብ፣ በተለይም ወጣቱ ትውልድ ያለ ድርጅታዊ አመራር የሚያካሂደው ትግል የትም እንደማያደርሰው ተገንዝቦ በተቃዋሚ ፓርቲዎች ዙሪያ በመሰባሰብና አስፈላጊውን ተሳትፎ በማድረግ፣ የሕዝቡን ትግል በአግባቡ የሚያስተባብርና የሚመራ ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ የመፍጠር ኃላፊነት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡ ኃላፊነቱ የመንግሥትም ጭምር መሆኑን አቶ ግዛቸው ጠቁመዋል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም ውስጣዊ ድክመታቸውን በመገምገም፣ ጥራት ባለው ሐሳብና ድርጅታዊ መዋቅር ራሳቸውን በማጠናከርና እርስ በርስ መጠላለፍና መናቆርን ትተው ኅብረትና ውኅደት መፍጠር እንዳለባቸውም አክለዋል፡፡
ፓርቲዎቹ አሁን ባሉበት ደካማ ድርጅታዊ አቅም (ኢዴፓን ጨምሮ) በገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ላይ ትርጉም ያለው ተፅዕኖ መፍጠርም ሆነ የሕዝብን ትግል በአግባቡ መምራት እንደማይችሉ የገለጹት አቶ ግዛቸው፣ ለራሳቸው መጠናከር ቅድሚያ በመስጠት ተግተው መሥራት እንዳለባቸውም አስረድተዋል፡፡ አጀንዳው ዕውን እንዲሆን ኢዴፓ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ የተናገሩት አቶ ግዛቸው፣ ‹‹አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ የፓርቲው ፕሮግራምና መተዳደርያ ደንብን ከማሻሻል ጀምሮ የፓርቲውን ስያሜ እስከመቀየርና የተናጠል ህልውናውን እስከማክሰም የሚደርስ ዕርምጃ በመውሰድ፣ አንድ ጠንካራ ፓርቲ በአገሪቱ የሚፈጠርበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ዝግጁ ነው፤›› ብለዋል፡፡
አቶ ልደቱ በበኩላቸው ጨምረው እንደተናገሩት የአገሪቱ ምሁራን ዳር ላይ ቆመው ከመታዘብና ከመተቸት ይልቅ፣ በሚያምኑባቸው ፓርቲዎች ዙሪያ ተሰባስበው ትግሉን በዕውቀታቸውና በገንዘባቸው የማጠናከር ሚና ሊጫወቱ ይገባል፡፡ ባለሀብቶችም ያለፖለቲካ መረጋጋት ያፈሩት ሀብትና ንብረት ዋስትና እንደሌለውና በአገር ላይ ሠርቶ መኖር እንደማይቻል በመረዳት፣ ሕጋዊና ሰላማዊ ትግሉን በሚችሉት ሁሉ በመርዳትና በማጠናከር ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የተፈጠረው የፖለቲካ ቀውስ ረግቦ ሕዝብ የሥልጣን ባለቤት የሚሆንበት እውነተኛ የብዙኃን ፓርቲ ሥርዓት አገር ለማድረግ፣ ኢዴፓ ተስፋ እንዳለው አቶ ልደቱ ተናግረዋል፡፡
የአገሪቱ የፖለቲካ ባህል ጽንፈኝነት የተጠናወተው በመሆኑ ከጽንፈኝነት ውጪ አማራጮችን ማየት እንደማይፈልግ የገለጹት አቶ ልደቱ፣ በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት በአገሪቱ የተከሰተው የፖለቲካ ቀውስ የመጣው በግራና በቀኝ ያለው የፖለቲካ ኃይል ጽንፈኛ በመሆኑ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዕጣ ፈንታ በአንድ ፓርቲ እንደማይፈታ የተናገሩት አቶ ልደቱ፣ በሚቀጥለው ዓመት በሚደረገው አካባቢያዊ ምርጫና ከሦስት ዓመታት በኋላ በሚደረገው አገራዊ ምርጫ፣ ፓርቲዎች ከወዲሁ ጠንክረው በመሥራትና ብቁ ተወዳዳሪ በመሆን የመድበለ ፓርቲ ሥርዓቱን ማጠናከር ተገቢ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የፖለቲካ ምኅዳሩ እጅግ በሚገርም ሁኔታ እየጠበበ መሆኑን ገዥው ፓርቲ ተገንዝቦ ካላስተካከለና ሁኔታዎችን ካላመቻቸ መጪው ጊዜ አስፈሪና ወደማያስፈልግ ሁኔታ ሊያመራ ስለሚችል መንግሥት ሁኔታዎችን በመመርመር፣ በማጥናትና በቀጣይ ሊከሰቱ የሚችሉ ነገሮችን አውቆ ብሔራዊ መግባባትን መፍጠር እንዳለበትም አቶ ልደቱ አሳስበዋል፡፡ ለነፃ፣ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ ምርጫ አስፈላጊ ነገሮችን ሁሉ ማመቻቸት እንዳለበትም አክለዋል፡፡ ‹‹የችግሩ ፈጣሪ እኔ ነኝ፣ የመፍትሔውም ሰጪ እኔ ነኝ፤›› ማለት ለኢሕአዴግ አያዛልቅም ብለዋል፡፡  

No comments:

Post a Comment

Related Posts Plugin for WordPress, Blogger...

Recent Articles

Recent Video Uploads

Subscribe Ethiopia Today Videos and Watch on You Tube

Ethiopia Today

  • Active a minute ago with many
  •  
  •  videos
Ethiopia Today bringing you recent information about Ethiopia. It bring you, news, Amharic movies,  Musics and many clips. subscribe and get many Videos on time